ለኬንያው ምርጫ በሕይወት የሌሉ ሩብ ሚሊዮን ድምጽ ሰጪዎች ተመዝግበው ተገኙ

ራይላ ኦዲንጋ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በቀጣዩ ምርጫ ተጠባቂ ተፎካካሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ
ታትሟል

ኬንያ ከሁለት ወራት በኋላ ለምታካሂደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሕይወት የሌሉ ከ250 ሺህ በላይ ድምጽ ሰጪዎች ተመዝግበው መገኘቱ ተገለጸ።

ኢንዲፔንደንት ኤሌክቶራል እና ባውንደሪስ ኮሚሽን የተሰኘው የኬንያው ገለልተኛ ምርጫ እና ሕዝበ ውሳኔ አስፈጻሚ ተቋም ባወጣው መግለጫ፤ የመራጮች ምዝገባ ላይ ባደረገው ምርመራ በሕይወት የሌሉ ሩብ ሚሊዮን ሰዎች ተመዝግበው አግኝቻለሁ ብሏል።

ከዚህ በተጫማሪም ለፕሬዝደንታዊው ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት መካከል ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉት ከአንድ ጊዜ በላይ ተመዝግበው ተገኝተዋል ብሏል።

ምርጫ እና ሕዝበ ውሳኔ አስፈጻሚ ተቋሙ 226 ሺህ ሰዎች ደግሞ የራሳቸው ባልሆኑ ሰነዶች ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል።

ድምጽ ለመስጠት ብቁ በማያደርጉ ሰነዶች የተመዘገቡ ድምጽ ሰጪዎች መኖራቸውንም ተቋሙ በመግለጫ አመላክቷል።

በጠቅላላው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ድምጽ ሰጪዎች ሕጋዊ አሰራርን ባልተከተለ መልኩ ድምጽ ለመስጠት ተመዝገበው ተገኝተዋል።

የተቋሙ ሊቀመንበር ዋፉላ ቼቡካቲ ሕጋዊ አሰራርን ባልተከተለ መልኩ መራጮች ተመዝግበው መገኘታቸው ተከትሎ ተቋማቸው የመጨረሻዎቹን መራጮች አረጋግጦ ይፋ የሚያደርግበትን ቀን ያራዝመዋል ብለዋል።

ገለልተኛ የሆነው ምርጫ እና ሕዝበ ውሳኔ አስፈጻሚ ተቋም የድምጽ ሰጪዎችን ዝርዝር አረጋግጦ ዛሬ ሐሙስ ይፋ ማድረግ ነበረበት።

በኬንያ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ማጭበርበሮች፣ ምርጫን ተከትሎ ለሚከሰቱ ሁከቶች አንዱ ምክንያት ነበር።

ኬንያ ነሐሴ 03/2014 ዓ.ም. ለምታካሂደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ እና ሥልጣን ላይ ያሉት ምክትል ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ መካከል ጠንካራ ፉክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአሁኑ ወቅት አገሪቱን እያስተዳደሩ ያሉት ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ሁለት የሥልጣን ዘመን በማገልገላቸው በምርጫው ተሳታፊ አይሆኑም።