ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ፣ ፑቲን ወደ ዩክሬን ጦርነት የገቡት ‘ተገደው’ ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን ላይ ወረራ የፈጸሙት “ተገደው” ነው በማለት ደግፈዋቸዋል።
የ85 ዓመቱ ቤርሉስኮኒ እንደሚሉት የሩሲያ ወታደሮች የዩክሬንን መንግሥት “በጨዋ ሰዎች” ተክተው ለመውጣት አስበው መሆኑንም ገልጸዋል።
ለሦስት ጊዜ ያህል የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ የሩሲያው ፕሬዝዳንት የረዥም ጊዜ ወዳጅ ናቸው።
በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ፓርቲያቸው በጣሊያን በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ የቀኝ ክንፍ ጥምረት አካል በመሆን ሥልጣን እንደሚይዝ ይጠበቃል።
የዩክሬን መንግሥት በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎችን እየገደለ ነው የሚል ትርክት በሞስኮ በመገናኛ ብዙኃን መፈብረኩን ቤርሉስኮኒ ለአንድ የጣሊያን ቲቪ ተናግረዋል።
በተገንጣይ ኃይሎች እና በብሔርተኛ ፖለቲከኞች የተስፋፋው ይህ ዘገባ ፑቲን ዩክሬንን ከመውረር በቀር ሌላ አማራጭ እንዳሳጣቸው ተናግረዋል።
“ፑቲን ይህን ልዩ ተልዕኮ ለመፈጸም በሩሲያ ሕዝብ፣ በፓርቲያቸው እና በሚኒስትሮቻቸው ተገፍተው ነበር” ብለዋል።
“ወታደሮቹ በአንድ ሳምንት ኪዬቭ ገብተው የዜሌንስኪን መንግሥት በማንሳት በጨዋ ሰዎች መተካት እና ከአንድ ሳምንት በኋላ ተመልሰው መውጣት ነበረባቸው” ሲሉ ቤርሉስኮኒ ተናግረዋል።
“ከምዕራቡ ዓለም በሁሉም ዓይነት የጦር መሳሪያዎች የሚደገፍ ያልተጠበቀ ተቃውሞ ገጠማቸው።”
ቤርሉስኮኒ የፑቲን አድናቂ መሆናቸው ይታወቃል። እአአ በ2012 ፑቲን ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በሩሲያዋ ሶቺ ከተማ ለበረዶ ሸርተቴ ስፖርት በጋራ አቅንተው ነበር።
በሚያዝያ ወር ወረራውን አውግዘው በፑቲን ባህሪ “በጣም እንዳዘኑ” ገልጸው፤ “በቡቻ እና በሌሎች አካባቢዎች በሠላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋም የጦር ወንጀል ነው” ብለው ነበር።
የፎርዛ ኢታሊያ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ቤርሉስኮኒ ከእሑዱ ጠቅላላ ምርጫ በፊት የቀኝ ክንፍ ጥምረት አካል በመሆን የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው።
የመሐል ቀኝ ፓርቲያቸው ከጂዮርጂያ ሜሎኒው ብራዘርስ ኦፍ ኢታሊ እና ከማቲዮ ሳልቪኒው ሌጋ ኖርድ ፓርቲ ጋር ኅብርት ፈጥሯል። ቀደም ተብሎ በተደረገ የሕዝብ አስተያየት ኅብረቱ አብላጫ ድምጽ እንደሚያሸንፍ ተጠቁሟል።
ቤርሉስኮኒ ከፑቲን ጋር የቀድመ ወዳጅነት አላቸው። ሳልቪኒ ደግሞ የምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ላይ የጣላቸውን ማዕቀቦችን ተችተዋል። መሪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ሜሎኒ ግን ጣሊያን ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይም “በዩክሬን ያለው ጦርነት የዓለምን ሥርዓት ለመለውጥ ያለመ ግጭት ነው። ስለዚህ ይህን ጦርነት መዋጋት አለብን” ሲሉ ተናግረዋል።












