የአምናው ሻምፒዮና ሲሳይን ጨምሮ ቀነኒሳ ስለሚሳተፉበት የለንደን ማራቶን በጥቂቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአለም ላይ ከሚጠበቁ የአትሌቲክስ ዝግጅቶች አንዱ የሆነው የለንደን ማራቶን በዛሬው ዕለት መስከረም 22፣ 2015 ዓ.ም እየተካሄደ ነው።
አምና አንደኛ በመውጣት ሻምፒዮና የነበረው ሲሳይ ለማን ጨምሮ በአትሌቲክስ ዘርፉ ስመ ጥር የሆነው ቀነኒሳ በቀለ ኢትዮጵያን ወክለው ለ42ኛ ጊዜ በሚካሄደው የለንደን ማራቶን ይወዳደራሉ። በሴቶች የማራቶን ውድድር ደግሞ በማራቶን ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት ያላት ያለምዘርፍ የኋላው ኢትዮጵያን ወክላለች።
በዛሬው ዕለት ወደ 42 ሺህ የሚጠጉ ሯጮች ከግሪንዊች አስከ ዘ ሞል ድረስ ድረስ ያለውን 42 ኪሎሜትር በመሸፈን ይሮጣሉ። በዚያውም ሚሊዮን ፓውንዶችን ለእርዳታ ያሰባስባሉ።
የዘንድሮው የማራቶን ውድድር በአውሮፓውያኑ ጥቅምት ወር የሚካሄደው ሶስተኛው እና የመጨረሻው ነው። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በጥቅምት ወር እንዲካሄድ ቢደረግም በሚቀጥለው ዓመት በአውሮፓውያኑ 2023 ወደተለመደው የጸደይ ወቅት ይመለሳል።
ስለ 2022 የለንደን ማራቶን በጥቂቱ
በውድድሩ እነማን ይሳተፋሉ?
የአራት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ሞ ፋራህ በዘንድሮው የማራቶን ውድድር ተስፋ ከተጣለባቸው አንዱ አትሌት መሆኑ ይዘገብ የነበረ ቢሆንም በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ባጋጠመው የዳሌ ጉዳት ምክንያት ራሱን አግልሏል። የሴቶች የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤትና በለንደን ማራቶን ሁለት ጊዘተ አሸናፊ ብሪጊድ ኮስጌይ ከውድድሩ ራሷን ለማግለል ተገዳለች።
ባለፈው ሳምንት በርሊን ላይ በራሱ ተይዞ የነበረውን የወንዶች ማራቶን የአለም ክብረ ወሰን የሰበረው ኢሊዩድ ኪፕቾጌ በዚህ ውድድር ባይሳተፍም ቅዳሜ በነበረው ሚኒ ማራቶን ውድድር ለአሸናፊዎች ሜዳሊያ ለማበርከት ለንደን ይገኛል።
ኪፕቾጌ በሌለበርት የአምናው የለንደን ማራቶን ሻምፒዮና ሲሳይ ለማ እና ሌላኛው ስመ ጥር አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በወንዶች የማራቶን ሻምፒዮናነት ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል ናቸው።
ሲሳይ ለማ የአምናውን የለንደን ማራቶን ያሸነፈው 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ 01 ሴኮንዶች በመግባት ነበር።
በማራቶን ታሪክ ሶስተኛው ፈጣን ሰአት ያለው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ብርሃኑ ለገሰ ዛሬ በለንደን ጎዳናዎች እየሮጠ ይገኛል።
ብርሃኑ በአውሮፓውያኑ 2019 በነበረው የበርሊን ማራቶን 2፡02፡48 በሆነ ሰዓት ቀነኒሳ በቀለን በመከተል ሁለተኛ መውጣቱ ይታወሳል። በዚህ ውድድር ላይ ሶስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው የአምናው የለንደን ማራቶን አሸናፊ ሲሳይ ለማ ነበር።
የሴቶች የማራቶን ወድድር ያለፈው አመት ሻምፒዮና ጆይሲሊን ጄፕኮስጌ እንዲሁም በማራቶን ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት ያላት ኢትዮጵያዊቷ ያለምዘርፍ የኋላው በውድድሩ ስፍራ ተሰጥቷቸዋል።
የሁለቱም የወንዶች እና የሴቶች ውድድር አሸናፊዎች እያንዳንዳቸው 55 ሺህ ዶላር የሚሸለሙ ሲሆን በዊልቸር ለሚወዳደሩ 35 ሺህ ዶላር ሽልማት ይሰጣቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጊነስና የባቡር የስራ ማቆም አድማ
በዘንድሮው የለንደን ማራቶን በአለም አቀፉ የድንቃ ድንቅ መዝገብ ጊነስ ለማስመዝገብ 28 ሙከራዎች እየተደረጉ ያሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል እንደ ጠርሙስ በመልበስ፣ ሁከቶችን ለመከላከል የሚደረጉ አልባሳት እንዲሁም በክራንች የሚወደዳሩ አሉ።በዚህ ውድድር ላይ የ89 አመቱ ጃፓናዊው ኮይቺ ኪታባታኬ የሚወደዳር ሲሆን እንግሊዛዊው አሌክስ ሆርስሌይ 18ኛ ልደቱን በማራቶን ውድድር ያከብራል። በዛሬው ውድድር ላይ አሌክስን ጨምሮ 205 ግለሰቦች ልደታቸውን በሩጫ ያከብራሉ።
ሆኖም በለንደን የተከሰተው የባቡር የስራ ማቆም አድማ ወደ ለንደን ለሚመጡ ተወዳዳሪዎች እንቅፋት እንደሆነ ተገልጿል።
በባቡር ሰራተኞች በታቀደው የስራ ማቆም አድማ ምክንያት የጉዞ መስተጓጎል የሚገጥማቸው ሯጮችን ለመርዳት "የምንችለውን ሁሉ" እያደረግን ነው” ብለዋል አዘጋጆቹ።
የባቡር አገልግሎቶች ቅዳሜ እለት አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበረ ሲሆን በዚህም ምክንያት ጥዋት ለሚደረገው ሩጫ በርካቶች ላይደርሱ ይችላሉ ብለዋል። የሩጫው ዳይሬክተር ሂዩ ብራሸር ለቢቢሲ ስፖርት እንደተናገሩት ዘግይተው የሚመጡ ሯጮች በኋላ እንዲጀምሩ ይፈቀድላቸዋል ብለዋል።












