የካናዳዋ ግዛት በሰደድ እሳት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አወጀች

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
በካናዳዋ ምዕራባዊ ግዛት ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ፣ በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣው ሰደድ እሳት በዌስት ኬሎውና ከተማ አካባቢ ተጨማሪ ቤቶችን ሊያወድም ይችላል በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ።
የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ግዛት አስተዳዳሪ ዴቪድ ኢቢይ ሁኔታው በፍጥነት እየተቀየረ እንደሆነና በሚመጡት ቀናትም በጣም ፈታኝ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የማክዱጋል ክሪክ ወንዝ ዳርቻ የተነሳው ይህ ሰደድ እሳት በ24 ሰዓት ውስጥ ከ64 ሔክታር ወደ 6 ሺህ 800 ሔክታር ተስፋፍቷል።
በዚህም ምክንያት 4 ሺህ 800 የሚሆኑ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
በሌላ በኩል በካናዳ ሰሜን ምዕራብ ግዛቶች በተቀሰቀሰ ሌላ የሰደድ እሳት 22 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
የካናዳ የፌደራል ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውን የሎውናይፍን ለቅቆ ለመውጣት የተቀመጠው ቀነ ገደብም ተጠናቋል።
ነዋሪዎችም በአየር እና በየብስ ከተማዋን ለቀው ለመውጣት ሲጣደፉ ቆይተዋል።
የሰደድ እሳቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በካናዳ ከተከሰቱት አስከፊው ነው ተብሏል።
የግዛቷ አስተዳዳሪ ኤቢይ አርብ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ "በዚህ ዓመት ከመቼውም ጊዜ የከፋውን ሰደድ እሳት እየተጋፈጥን ነው” ብለዋል።
የሰደድ እሳቱ በፍጥነት እየተዛመተ በመሆኑም በግዛቷ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ማስፈለጉንም ገልጸዋል።
አስተዳዳሪው ጨምረውም "ይህ ነዋሪዎችን ለመደገፍ የሚያስፈልጉንን ማናቸውንም ድጋፎች በፍጥነት ለማድረስ የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆናችንን ያረጋግጥልናል" ብለዋል።
በርካታ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መደረጉን የገለጹት አስተዳዳሪው፣ነዋሪዎች አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዞዎችን እንዳያደርጉ ያቀረብነውን ጥሪ ካላከበሩ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተወሰኑ ቦታዎች የጉዞ ገደብን ሊያካትት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ቀደም ብሎ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ውስጥ የምትገኘው ዌስት ክሎውና ከተማ የእሳት አደጋ ኃላፊ ጃሰን ብሮለንድ የሰደድ እሳቱን "አውዳሚ" ሲሉ ገልጸውታል።
በክሎና ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያለው የአየር ክልልም ከእሳት አደጋ አውሮፕላኖች በስተቀር ለሁሉም አገልግሎት ዝግ እንዲሆን ተደርጓል።












