በዴሞክራቲክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ውስጥ ጎርፍ ከ120 በላይ ሰዎችን ገደለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዓመታት ውስጥ ከታዩት ሁሉ የከፋው ነው የተባለ የጎርፍ አደጋ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ ውስጥ ከ120 በላይ ሰዎችን መግደሉን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ከባድ ዝናብ ለሰዓታት ከዘነበ በኋላ የከተመዋ ዋና አውራ ጎዳኖች በውሃ ሲዋጡ፣ መኖሪያ ቤቶች ደግሞ በጎርፍ ተወስደዋል።
እንደ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ከሆነ አብዛኛው ሟቾች በተራራማ ቦታ ይኖሩ የነበሩ እና በመሬት መንሸራተት ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ናቸው።
በጎርፉ አደጋ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ከተሰማ በኋላ የአገሪቱ መንግሥት ለሦስት ቀናት የሚዘልቅ ብሔራዊ የሐዘን ጊዜ አውጇል።
የፈረንሳዩ ዜና ወኪል የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ጋዜጠኛ መኖሪያ ቤታቸው ከፈረሰ በኋላ ሕይወታቸው ያለፈ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የዘጠኝ ሰዎችን አስክሬን ተመልክቷል።
ጉዳቱ ባጋጠመበት ቦታ ነዋሪ የሆኑት በላንቻርድ ቩቡ “በዚህ ደረጃ ጎርፍ አይተን አናውቅም” ብለዋል።
“ተኝቼ ነበር። ጎርፍ ቤት ውስጥ ሲገባ ታወቀኝ። ከባድ ውድመት ነው። ሁሉም ንብረታችንን አጥተናል። ቤታችን እና ምንም ንብረት አልተረፈንም” ብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጄን-ሚቼል ሳማ ሉኮንዴ አስተዳደር ልዑካን ያጋጠመውን ጉዳት ለመመልከት ወደ ኪንሻሳ አካባቢዎች አቅንተዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በአደጋው ሳይሞቱ አይቀርም የተባሉ የተጨማሪ ሰዎች አስክሬን እየተፈለገ መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ለደረሰው ጉዳት የአየር ለውጥ ምክንያት ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።
“ዴሞክራቲክ ኮንጎ ጫና ውስጥ ናት ይሁን እንጂ በአግባቡ አልተደገፈችም ወይም አልተደመጠችም” ሲሉ ለአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ዋሽንግተን የሚገኙት ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴክዲ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ለአየር ብክለት ተጠያቂ የሆኑ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ የሚሰቃዩ አገራትን ለመርዳት ብዙ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ቲሺሴክዲ የዋሽንግተን ዲሲ ቆይታቸውን በማሳጠር ወደ አገራቸው ሊመለሱ ይችላሉ ብለዋል።
በአፍሪካ አሜሪካ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የዲሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት፣ ከአሜሪካው አቻቸው ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በአደጋው ምክንያት ሐሙስ ዕለት ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በኮንጎ ወንዝ ዳርቻ የምትገኘው ኪንሻሳ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የነዋሪዋ ቁጥር በከፍተኛ መጠን የጨመረ ሲሆን አሁን ላይ ከ15 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እየኖረ ይገኛል።
በርካታ ሰዎች ጠንካራ መሠረት በሌላቸው እና እርስ በእርሳቸው በተያያዙ እና ለጎርፍ አደጋ በተጋለጡ ቦታዎች ይኖራሉ። መዲናዋም ይህ ነው የሚባል የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት የላትም።












