ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖላንድ የተመታችው በዩክሬን ሚሳኤል እንደሚሆን ኔቶ ገለጸ
ፖላንድ ውስጥ ሁለት ሰዎችን የገደለው ሚሳኤል የዩክሬን ሊሆን እንደሚችል የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ዋና ጸሐፊ የሆኑት ጀነራል ጄን ስቶልንበርግ ለቢቢሲ ገለጹ።
በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ስለተተኮሰው ሚሳኤል ምርመራ እየተደረገ ሲሆን፣ ዋና ጸሐፊው “ሚሳኤሉ የዩክሬን የአየር መከላከያ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው” ብለዋል።
ሚሳኤሉ የዩክሬን ቢሆንም፣ ለአጠቃላይ ሁኔታው ተጠያቂ ወረራ ያካሄደችው ሩስያ እንደሆነች ተናግረዋል።
ሚሳኤሉ የተተኮሰው በሩሲያ እንደሆነ ዩክሬን ገልጻለች።
“ይሄ የኛ ሚሳኤል እንዳልሆነ ቅንጣት አልጠራጠርም። ወታደራዊ ሪፖርቶቻችን እንደሚያሳዩት ሚሳኤሉ የሩሲያ ነው” ሲሉ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ከዩክሬን ድንበር በስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣ በፖላንድ፣ ፕርዝዎዶ በተባለ የእርሻ ቦታ የወደቀው ሚሳኤልን በተመለከተ በሚደረገው ምርመራ ለመሳተፍ ዩክሬን ጠይቃለች።
ሩሲያ ባለፈው ማክሰኞ ከዘጠኝ ወራት በፊት የዩክሬን ወረራ ከተጀመረ ወዲህ ትልቁ የተባለ ተከታታይ የሚሳኤል ድብደባ ዩክሬን ላይ ፈጽማለች።
ይህንን ተከትሎም ማክሰኞ የዩክሬን የአየር መከላከያዎች አልግሎት እየሰጡ ነበር።
ሩሲያ በርካታ ሚሳኤሎችን ብትተኩስም ዩክሬን መታ እንደጣለቻቸው አስታውቃለች።
የቡድን 20 አገራት ጉባዔ በኢንዶኔዥያ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው ሩሲያ ጥቃቱን የፈጸመችው።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ጥቃቱን አውግዟል።
የኔቶ አባል በሆነችው ፖላንድ ውስጥ ሚሳኤል መተኮሱ ጦርነቱ በአስጊ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ይጠቁማል ተብሎም ተፈርቷል።
የኔቶ ዋና ጸሐፊ እንዳሉት፣ ኔቶ ዘመነኛ የአየር መከላከያዎችን ለዩክሬን ለመስጠት ቃል ገብቷል።
“ዩክሬንን ከሚደግፉ የኔቶ አጋሮች ጋር ባደረግነው ውይይት ዘመናዊ የአየር መከላከያ መሣሪያዎችን ለመስጠት ተስማምተናል። መሣሪያዎቹ የሩሲያን ሚሳኤል መተው ይጥላሉ” ብለዋል።
ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው ግን ጦርነቱን ማቆም እንደሆነ ዋና ጸሐፊው አስምረውበታል።
የፖላንድ ፕሬዝዳንት አንድርዜጅ ዱዳ፣ ከጥቃቱ ጀርባ ያለው S-300 የተባለው የሩሲያ ሚሳኤል እንደሆነ ተናግረዋል።
ሆኖም ግን የተሰነዘረው ከሩሲያ እንደሆነ ማስረጃ አልተገኘም።
ዩክሬን እና ሩሲያን ለማስታረቅ ስለሚደረገው ጥረት የተጠየቁት የኔቶ ዋና ጸሐፊ “ፑቲን ለመደራደር ፈቃደኛ አልሆኑም። ፑቲን ጦርነቱን ለማቆም ከፈቀዱ ሰላም ይሰፍናል። ዩክሬን ራሷን መከላከል ካቆመች ግን ውድመት ይጠብቃታል” ብለዋል።
ሩሲያ ከዩክሬን መውጣቷ ለጦርነቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ወደመስጠት ሊያመራ እንደሚችል አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ጄነራል ተናግረዋል።
ሆኖም ግን ሌላኛው ወታደራዊ ጀነራል ማርክ ሚሊ እንዳሉት፣ ዩክሬን አጠቃላይ ግዛቶቿን አስመልሳ ድል የምትቀዳጅበት ጊዜ ሩቅ ሊሆን ይችላል።