በቴህራን እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ የጸጥታ ኃይሎች ከተማሪዎች ጋር መጋጨታቸው ተገለጸ

ታትሟል

ትናንት እሁድ የኢራን ፖሊስ በአገሪቷ ከሚገኙ እውቅ ዩኒቨርሲቲዎች በአንዱ ውስጥ ከሚማሩ ተማሪዎች ጋር መጋጨቱን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እና በማኅበራዊ ሚዲያ የወጡ ሪፖርቶች አመለከቱ።

ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በቴህራን በሚገኘው ሻሪፍ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ በሚገኝ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ እንቅስቃሴያቸው ተገድቧል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ቪዲዮዎች ተማሪዎች ከጸጥታ ኃይሎች እና ከተኩስ ለማምለጥ ሲሯሯጡ አሳይተዋል።

በኢራን አንዲት ወጣት እስላማዊ ሥነ ምግባርን ጥሰሻል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ መሞቷን ተከትሎ ነበር መስከረም ወር ላይ ፀረ መንግሥት ተቃውሞ የተቀሰቀሰው።

የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ፣ ፀጉርሽን አልሸፈንሽም በሚል የሥነ ምግባር ተቆጣጣሪ ፖሊስ ካሰራት በኋላ ለሰዓታት ያህል 'ኮማ' ውስጥ ሆና ቆይታለች።

የፖሊስ መኮንኖቹ አሚኒን ጭንቅላቷን በዱላ እንደደበደቧት እና ጭንቅላቷን እየጎተቱ ከመኪናቸው ጋር እንዳጋጯት ተዘግቧል።

ፖሊስ ግን አሚኒ ላይ ተፈፀመ የተባለውን ድርጊት የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም ያለ ሲሆን በድንገተኛ የልብ ሕመም ስትሰቃይ ነበር ብሏል።

ከዚያም በቀብር ሥነ ሥርዓቷ ላይ ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን ተቃውሞው በመላ አገሪቷ ተስፋፍቶ በዓመታት ውስጥ ያልታየ ከፍተኛ አለመረጋጋትን ፈጥሯል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተጋራው ቪዲዮ፣ በሻሪፍ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ተማሪዎች ከጸጥታ ኃይሎች ለማምለጥ ሲሯሯጡ ታይተዋል። በዚሁ ቪዲዮ ላይ የጥይት ተኩስ የሚመስልም ድምጽም ከርቀት ይሰማል።

በሌላ ቪዲዮ ላይ ደግሞ የጸጥታ ኃይሎች በሞተር ሳይክል ሆነው በመኪና ውስጥ ሆኖ ቪዲዮውን ሲቀርጽ የነበረ መንገደኛን ያሳፈረ መኪና ላይ ሲተኩሱ ታይተዋል።

ዋና መሥሪያ ቤቱን በለንደን ያደረገው ኢራን ኢንተርናሽናል፣ የጸጥታ ኃይሎች የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች ላይ ጥቃት መክፈታቸውንና በማደሪያ ክፍሎቻቸው ላይ ጥይት መተኮሳቸውን የሚያሳዩ ሪፖርቶች መኖራቸውን ጠቅሷል።

ሌሎች ደግሞ በተቃዋሚዎቹ ላይ አስለቃሽ ጭስ ጥቅም ላይ መዋሉን ዘግበዋል።

እሁድ እለት ለመጀመሪያ ጊዜ ሻሪፍ ዩኒቨርሲቲ የገቡ በርካታ ተማሪዎች ትምህርት የጀመሩበት ቀን ነበር።

ግጭቱ ከተሰማ በኋላም የዚያኑ እለት ምሽት ከዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ ደጅ ላይ በርካታ ሰዎች ተሰባስበው እንደነበር ሪፖርቶች አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ ቢቢሲ በዩኒቨርሲቲው ስለነበረው ሁኔታ ማረጋጋጥ አልቻለም።

ባለፉት ሁለት ምሽቶችም በቴህራን እና በሌሎች ከተሞች እየተካሄደ ያለው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የሚሞቱ ሰዎችም ቁጥር ጨምሯል።

ተቀማጭነቱን በኖርዌይ ያደረገው የኢራን የስብዓዊ መብቶች ድርጅት እንዳለው እስካሁን 133 ሰዎች ተገድለዋል።