የናይጄሪያ የምክር ቤት አባል የሰው ኩላሊት ለልጃቸው በመግዛት ወንጀል ጥፋተኛ ተባሉ

የተከበሩ ሴናተር ኢኬ ኢኬዌረማዱ ባለሀብት ናቸው

የፎቶው ባለመብት, MET POLICE

የምስሉ መግለጫ, የተከበሩ ሴናተር ኢኬ ኢኬዌረማዱ ባለሀብት ናቸው
ታትሟል

አንድ የናይጄሪያ ባለሃብት እና የምክር ቤት አባል የሆኑ ግለሰብ እንዲሁም ባለቤታቸው የሰውን አካል በመግዛት ወንጀል ጥፋተኛ ተባሉ።

የተከበሩ ሴናተር ኢኬ ኢኬዌረማዱ እና ባለቤታቸው ቢያትሪስ ይህን ወንጀል ሲፈጽሙ የነበረው ኦቢና ኦቤታ ከተባለ አንድ የሕክምና ዶክተር ጋር በመመሳጠር ነበር።

ሦስቱ የወንጀል ጥምረት የፈጠሩት ግለሰቦች አንድን የ21 ዓመት ወጣት ከሌጎስ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በማሻገር አዲስ ሕይወት ትጀምራለህ በሚል ተስፋ ኩላሊቱን በንቅለ ተከላ ለልጃቸው ለማስተላለፍ መመሳጠራቸው ተደርሶበታል።

የገዛ ኩላሊቱ ሊሸጥበት የነበረው ወጣት የጎዳና ንግድ ላይ የተሰማራ ናይጄሪያዊ ሲሆን፣ ወደ ዩኬ የተወሰደው 80ሺህ ፓውንድ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንደሚሰጡት ቃል ተገብቶለት ነው።

ይሁንና ኩላሊት ሊወሰድበት እንደሆነ አልተብራራለትም ተብሏል።

ኩላሊት ሊሰጣት የነበረችው ሴት የ25 ዓመቷ ሶንያ ስትሆን፣ የኚህ የተከበሩ የምክር ቤት አባል እና ባለሐብት ሴት ልጅ ናት። የምትኖረውም በዳያለሲስ ነው።

የኩላሊት ንቅለ ተከላው ሊደረገው የነበረው በለንደን የሮያል ፍሪ ሆስፒታል ውስጥ ነበር።

በሌጎስ የጎዳና ላይ ንግድ ላይ የነበረው ወጣት ስለ ኩላሊቱ ንቅለ ተከላ ምንም ዓይነት መረጃ ሳይሰጠው በመቅረቱ ሆስፒታል ውስጥ ሲደነጋገር ነበር ተብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወደ ለንደን ተወስደህ አዲስ ሕይወት ትጀምራለህ የተባለው ወጣት ለጊዜው ቃል የተገባለት 7ሺህ ፓውንድ ተሰጥቶት ነበር።

ወጣቱ የገዛ ኩላሊቱ ሊወሰድበት እንደሆነ ያወቀው ግን ሆስፒታል ከሐኪም ጋር ሲገናኝ ነበር።

እኚህ የተከበሩ የምክር ቤት አባል ግን ግለሰቡ የልጃቸው የሶኒያ የአክስት ልጅ እንደሆነ ሐኪሞቹን ለማሳመን ጥረት አድርገዋል ተብሏል።

ምን እንደተደገሰለት ያለወቀውን ወጣት ለማሳመን በእርሱ እና በሐኪሞቹ መካከል የቆሙ አስተርጓሚዎች ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሏቸውም ነበር ተብሏል።

ይሁንና ሐኪሞች የወጣቱ ሁኔታ ጥርጣሬን ፈጥሮባቸዋል።

በዩኬ ምንም እንኳ ኩላሊትን በፈቃደኝነት መለገስ ሕጋዊ አሠራር ቢሆንም በገንዘብ የሰውን አካል መግዛትና መሸጥ ግን ከባድ ወንጀል ነው።

በዕለቱ የሮያል ፍሪ ሆስፒታል ሐኪም ዶ/ር ፒተር ደፖንት ግለሰቡ ለንቀለ ተከላው ዝግጁ እንዳልሆነ በመረዳታቸው ቀዶ ጥገናው እንዲዘገይ ወስነዋል።

ወጣቱ ከዚህ በኋላ ከሆስፒታል ሮጦ አምልጦ ለሦስት ቀናት በለንደን ጎዳና ላይ እያደረ ቆይቶ በመጨረሻ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ደርሶ እያለቀሰ ሁኔታውን በመንገሩ ነው ወንጀሉ ሊደረስበት የቻለው።

ይህንን የወንጀል ድርጊት በዩኬ ውስጥ የተመለከተው ችሎት በዘመናዊ ባርነት ሕግ (modern slavery act) ሦስቱን ግለሰቦች ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

ኩላሊት ሊሰጣት የነበረችው ሶኒያ ኡኬሩዎማዱ ከወንጀል ነጻ በተባለችበት ቅጽበት፣ ወንጀለኛ የተባሉትን አባቷን አቅፋ አምርራ ስታለቅስ ታይታለች።

ይህን ወንጀል ያቀነባበረው ዶ/ር ኦቢና ኦቤታም ጥፋተኛ ተብሏል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ለተመሳሳይ ንቅለ ተከላ ቱርክ ተጉዘው ሲመለሱ ነው።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት በዐቃቤ ሕግ የቀረቡለትን ተጠርጣሪዎቹ በዋትስአፕ ሲለዋወጧቸው የነበሩ የአጭር የጽሑፍ መልዕክቶችን መርምሯል።

ጥፋተኛ የተባሉት ሦስቱ ግለሰቦች የእስር ብይን በግንቦት ወር ይጠበቃል።

በዚህ የሰው ሰውነት ንግድ የተሳተፉ ሰዎች በዚህ በዩኬ ታሪክ የመጀመሪያ ነው በተባለው የዘመናዊ ባርነት ወንጀል ሲዳኙ የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ፣ ፍርድ ቤት እስከ ዕድሜ ልክ ሊፈረድባቸው ይችላል ተብሏል።