በባንግኮክ አየር ማረፊያ ውስጥ አደጋ የደረሰባቸው መንገደኛ እግራቸውን አጡ

ግለሰቧ በመረማመጃ ማሽኑ ተይዘው

የፎቶው ባለመብት, DON MUEANG INTERNATIONAL AIRPORT

የምስሉ መግለጫ, የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሴትየዋን እግር ከተንሸራታች የመረማመጃ ማሽኑ ውስጥ ማውጣት ስላልቻሉ የታችኛውን የእግራቸውን ክፍል መቆረጥ ግዴታ ሆኖ ነበር
ታትሟል

ታይላንድ ባንግኮክ አየር ማረፊያ ውስጥ በሚገኝ ተንሸራታች መራመጃ ላይ አንድ እግራቸው የተያዙ ሴትን ለማትረፍ በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እግራቸው ተቆረጠ።

ዶን ሙዩንግ በተባለው አየር ማረፊያ ለጉዞ የተገኙት የ57 ዓመቷ ሴት፣ ሻንጣ አደናቅፏቸው ሲወድቁ እግራቸው በተንሸራታች መረማመጃ ውስጥ ተይዞ ለማውጣት አስቸጋሪ በመሆኑ ነበር እግራቸውን መቁረጥ ግዴታ የሆነው።

ሐሙስ ዕለት ካጋጠመው ክስተት በኋላ ለግለሰቧ ቀዶ ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን፣ ቤተሰባቸውም በተፈጠረው ሁኔታ በእጅጉ መደናገጡን ልጃቸው ገልጾ፣ የአእምሮ ጤናቸው ሁኔታም እንዳሳሰባቸው ተናግሯል።

በድንገተኛ እና በማይጠበቀው አደጋ እግራቸውን ያጡት ግለሰብ ልጅ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው “የእናቴ የአእምሮ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው” ብሏል።

“ቀዶ ህክምናው ከመደረጉ በፊት እና በኋላ አናግረናት ነበር…ምንም እንኳን በፊት ገጽታዋ እና በድምጿ ጥንካሬዋን ልታሳየን ብትሞክርም፤ በድንገት እግሯን በማጣቷ ውስጧ ክፉኛ እንደተጎዳ እንረዳለን” ሲል ልጃቸው ኪት ኪቲራታና ጽፏል።

ጨምሮም “ቤተሰባችን መልሳ በእግሯ እንድትቆም ወይም በፊት የነበራት ሕይወት እንዲመለስ ማድረግ እንደማይችል ይረዳል” በማለት የእናታቸው ቀጣይ ሕይወት እንደሚያሳስባቸው ገልጿል።

አደጋው የደረሰባቸው ስማቸው ያልተገለጹት ሴት ግራ እግር በተንሸራታች መራመጃው ማሽን ውስጥ ተይዞ እሳቸውም ተቀምጠው የሚያሳዩ መስሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ታይተዋል።

አጠገባቸው የነበረ ሮዝ ቀለም የለው ትንሽዬ ሻንጣም ሁለት ጎማዎቹ በተንሸራታቹ መረማማጃ የተቆረጠ ሲሆን እንዲሁም ሌሎች ቁሶች መሰባበራቸው ተመልክቷል።

የአየር ማረፊያው አስተዳዳሪዎች በተከሰተው አደጋ “በእጅጉ ማዘናቸውን” ገልጸው፣ በግለሰቧ ላይ ለደረሰው የአካል ጉዳት ካሳ እንደሚከፍሉ እና የህክምና ወጪያቸውን እንደሚሸፍኑ አሳውቀዋል።

የአየር ማረፊያው ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ካራንት ታናኩሊጂራፓት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በግለሰቧ ላይ ድንገተኛ ጉዳትን ያደረሰው አደጋ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ ነው።

ጨምረውም አየር ማረፊያው በርካታ ያረጁ ተንሸራታች መረማመጃዎችን ከሁለት ዓመት በኋላ ለመቀየር ዕቅድ የነበረው ሲሆን፣ ይህ ክስተት ዕቅዱን በቶሎ ተግባራዊ እንዲያደርግ ሳያስገድደው አይቀርም።

የታይላንድ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት አደጋ ያደረሰው ተንሸራታች የመረማመጃ ማሽን ከአውሮፓውያኑ 1996 ጀምሮ ከ25 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ነው።