ተመድ እና የአውሮፓ ኅብረት የተቃወሙት ትዊተር በጋዜጠኞች ላይ የጣለውን ዕገዳ አነሳ

መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ስለቢሊየነሩ የትዊተር ባለቤት የተለያዩ መረጃዎችን አጋርተዋል በሚል የተዘጉ የበርካታ ጋዜጠኞች የትዊተር አካውንት እንደሚከፈት ኤሎን መስክ ገለጸ።

ይህንን የቢሊየነሩን ውሳኔን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት እና የአውሮፓ ኅብረት እርምጃውን አጥብቀው ካወገዙ በኋላ ነው ውሳኔው እንደሚቀለበስ የተገለጸው።

በእርምጃው የማኅበራዊ ሚዲያውን የተመለከተ ዘገባ የሠሩ የኒው ዮርክ ታይምስ፣ የሲኤንኤን እና የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኞች ከገጹ ታግደዋል።

ነገር ግን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ውግዘት እና ተቃውሞ በሚሰማበት ጊዜ ኤሎን መስክ የትዊተር ተጠቃሚዎችን በውሳኔው ድምጽ እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

በዚህም ሠረት ድምጽ ከሰጡት 3.6 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 59 በመቶዎቹ በጋዜጠኞቹ ላይ የጣለውን ከትዊተር ማገድ እርምጃ በቶሎ እንዲያነሳ ጠይቀዋል።

ይህንንም ተከትሎ ኤሎን መስክ የእራሱን የበረራ እንቅስቃሴ እየተከታተለ ይፋ ከሚያደርገው ገጽ በስተቀር ሌሎቹ እንደሚከፈቱ አሳውቋል።

የመስክን ጋዜጠኞችን የማገድ ውሳኔን ያወገዙት የመንግሥታቱ ድርጅት እና የአውሮፓ ኅብረት እርምጃው እንዳሳሰበቻውና በዝምታ እንደማይመለከቱት ገልጸው ነበር።

“የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት በዋዛ የሚታይ አይደለም” ሲል የመንግሥታቱ ድርጅት ትዊት አድርጓል። የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ ትዊተር ላይ ማዕቀብ ለመጣል ዝቷል።

የትዊተር ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ ጋዜጠኞቹ የታገዱት ሰዎች ያሉበትን ቦታ ከማጋራት ጋር በተያያዘ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ፀሐፊት መሊሳ ፍሌሚንግ “ጋዜጠኞች በዘፈቀደ ከትዊተር መታገዳቸው አሳስቦናል። ጋዜጠኝነት ዴሞክራሲ እንዲያብብ እና ሐሰተኛ መረጃ እንዲገታ ቁልፍ ሚና አለው” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነር ቬራ ጆሮቫ ትዊተር በአዲሱ የአውሮፓ ዲጂታል ሕግ መሠረት ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል ገልጸዋል።

“የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት መሠረታዊ ነጻነት ነው። ኤሎን መስክ ይህን መገንዘብ አለበት። በቅርቡ ማዕቀቦች ይጣላሉ” ብለዋል።

መስክ እስካሁን በይፋ ምላሽ ባይሰጥም “እኔን መተቸት ትችላላችሁ። ያለሁበትን ቦታ በመግለጽ ቤተሰቤን ለአደጋ ማጋለጥ ግን አትችሉም። ጋዜጠኞች እንደማንኛውም ሰው በመርኅ ነው መሥራት ያለባቸው” ብሏል።

መስክ የታገዱት ጋዜጠኞች ገጻቸው በአፋጣኝ ይከፈት ወይስ ቆይቶ ይከፈት ሲል የትዊተር ተጠቃሚዎችን ድምጽ ሰብስቧል።

የኒው ዮርክ ታይምስ ቃል አቀባይ እገዳውን “ጥያቄ የሚያጭርና አሳዛኝ ክስተት” ሲሉ ገልጸውታል።

ከጋዜጠኞች ጋር ውዝግብ ውስጥ ከመግባቱ በፊት፣ የግል ጀቱን እንቅስቃሴ እየተከታተለ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ የትዊተር ገጽ ባለቤት ላይ ክስ እንደሚመሠርት የማኅበራዊ ትስስር መድረኩ ባለቤት መስክ ገልጾ ነበር።

ይህ ሰው ባጋራው መረጃ ምክንያት ልጁ ለአደጋ እንደተጋለጠም መስክ መናገሩ አይዘነጋም።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ዘገባ የሠሩ ጋዜጠኞችን የትዊተር ገጽ መዝጋቱ አነጋጋሪ ሆኗል።

መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ከገዛ በኋላ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ስሙ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

ሠራተኞችን ከሥራ መቀነስ እና የሥራ ጫና ማብዛት ከእነዚህ መካከል ናቸው።

ትዊተርን የገዛው የመናገር ነጻነትን ለማበረታታት እንደሆነ ቢናገርም፣ እየወሰዳቸው ያሉትን እርምጃዎቹን የመብት ተሟጋቾች እየተቹ ነው።

መስክ የወሰዳቸው እርምጃዎች የንግግር ነጻነትን የማይደግፉ፣ ጥቃትን የሚያባብሱና ለሐሰተኛ መረጃ ስርጭት መንገድ የሚከፍቱ እንደሆኑ ተተችቷል።

የአውሮፓ ኅብረት መስክ ላይ ማዕቀብ ሊጥል የሚችለው በአዲሱ የበይነ መረብ ሕግ (Digital Services Act) አማካይነት ነው።

ኅብረቱ እስከ 6 በመቶ የሚደርስ የትዊተር ዓለም አቀፍ ገቢውን ላይ ቅጣት የመጣል ውሳኔን ሊያሳልፍ ይችላል።

“ለሰዎች ሕይወት እና ደኅንነት አደጋ ናቸው” የተባሉ አሠራሮችን እንዲያስተካክል በፍርድ ቤት ታዞ ሳይፈጽም ከቀረ ገጹን እስከማገድ ይደርሳሉ።

ገጻቸው ከታገደባቸው ጋዜጠኞች አንዱ ማት ቢንደር “በእርግጥ በዘገባዬ መስክን ተችቻለሁ። ከዚያ ውጪ ግን የታገዱት ጋዜጠኞች ያለሁበትን ቦታ ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል የሚለው ነገር ፍጹም ከእውነት የራቀ ነው” ብሏል።

የመስክን የግል ጀት እንቅስቃሴ የሚከታተለው የትዊተር ገጽ ባለቤት ላይ ስለሚመሠረተው ክስ ጋዜጠኛው ሲጽፍ፣ ወደ ግለሰቡ የትዊተር ገጽ የሚያመራ ማስፈንጠሪያ አለማስገባቱን ገልጿል።

“ወደ ትዊተር ገጹ የሚወስዱ ማስፈንጠሪያዎች ትዊት ያደረጉ ሰዎች ብዙ ናቸው። ጋዜጠኞቹ ግን ተመርጠው ነው ገጻቸው የተዘጋው” ሲል ተናግሯል።

በሌላ በኩል ኤንቢሲ ኒውስ፣ ቤን ኮለንስ የተባለ የሐሰተኛ ዘገባ ቁጥጥር ዘጋቢውን ከሰሞኑ ከሥራ ያገደው መስክን በመተቸቱ እንደሆነ ተገልጿል።

መስክ የአንዳንድ ተጠቃሚዎችን የትዊተር ገጽን ከገዛ በኋላ እንደ አማራጭ ማኅበራዊ ሚዲያ የመጣው ማስቶዶን ሲሆን፣ የዚህ መተግበሪያ የትዊተር ገጽም ታግዷል።

የማስቶዶን ገጻቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ የጻፉ የትዊተር ተጠቃሚዎች ገጽ ላይ “ለአደጋ የተጋለጠ” የሚል ማሳሰቢያ ተለጥፏል።