የማዳጋስካር ፖሊስ 19 ሰልፈኞችን ተኩሶ ገደለ

የማዳጋስካር ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የማዳጋስካር ፖሊስ
ታትሟል

በደቡብ ምስራቅ ማዳጋስካር ኢኮንጎ ከተማ አንድ አልቢኖ ህፃን መታገቱን ተከትሎ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ፖሊስ በተኮሰው ጥይት በትንሹ 19 ሰዎች ሲገደሉ 21 ሰዎች ቆሰሉ።

ባሳለፍነው ሰኞ በተፈጠረው በዚሁ ክስተት ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአካባቢው ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

እገታውን አከናውነዋል ተብለው የተጠረጠሩ አራት ሰዎች ወደታሰሩበት ፖሊስ ጣቢያ 500 የሚጠጉ ሰዎች ገጀራ ይዘው ለመግባት ሞክረው እንደነበረም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ አንድሪ ራኮቶንድራዛካ ፖሊሶች ግጭቱን ለማስቀረት ሞክረው ባለመሳካቱ ራሳቸውን ለመከላከል ወስነዋል ሲሉ የፖሊስን እርምጃ ምክንያታዊ ነው ሲሉ ለማብራራት ሞክረዋል።

ነገር ግን ጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል።

በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የአልቢኖ ችግር ያለባቸው ሰዎች የአካል ክፍሎቻቸው ዕድል እና ሀብት ሊያመጡ ይችላሉ በሚል የተሳሳተ እምነት የጥቃት ኢላማ ይሆናሉ።

አልቢኖ ጥቁር ቆዳ ባላቸው ሰዎች ላይ በጣም ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም ሁሉንም የሰው ልጆች ሊያጠቃ ይችላል።

የታገተው ህጻን ያለበት ሁኔታ ብሎም እጣ ፈንታ ግልጽ ባይሆንም እናቱ ግን በሽፍቶች ተገድላለች ሲሉ የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።