ሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያው ሰው በኮቪድ ምክንያት ሕይወቱ አለፈ አለች

ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ ሰው የመጀመሪያው ሰው ተመዘገበ አለች።

ከዚህ በተጨማሪ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ደግሞ ከኮቪድ 19 ምልክቶች አንዱ የሆነው ትኩሳት አንደታየባቸው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

መገናኛ ብዙኃኑ እንደዘገበው በከባድ ትኩሳት 6 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ አንድ ግለሰብ ግን የኦሚክሮን ቫይረስ ከተገኘበት በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

በተጨማሪም 187 ሺህ ሰዎች ትኩሳት አጋጥሟቸው ራሳቸውን አግልለው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ መገናኛ ብዙኃኑ አክሏል።

ባለሥልጣናት የመጀመሪያ ነው ያሉትን በኮቪድ የተያዘ ሰው መመዝገቡን ሐሙስ ዕለት ቢያሳውቁም፤ ባለሙያዎች ግን ቫይረሱ ለተወሰነ ጊዜ በአገሪቷ ውስጥ እንደነበር ያምናሉ።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የኮሮናቫይረስ ዝርያ የሆነው ኦሚክሮን ወረርሽኝ በዋና መዲናዋ ፒዮንግያንግ ተከስቶ ነበር።

ይሁን እንጂ ምን ያህል ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ በአሃዝ አልጠቀሱም።

አርብ ዕለት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሆነው ኮሪያ ሴንትራል ኒውስ ኤጀንሲ (ኬሲኤንኤ) ወረርሽኙ ወደ ሌሎች ቦታዎች መዛመቱን ዘግቧል። "ከሚያዝያ መጨረሻ አንስቶ ምክንያቱ ያልታወቀ ትኩሳት በመላ አገሪቷ ተሰራጭቷል" ብሏል።

መገናኛ ብዙኃኑ እስካሁን ምን ያህል ሰዎች በኮቪድ እንደተያዙ ሳይጠቅስ ወደ 350 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ግን የትኩሳት ምልክት እንደታየባቸው ገልጿል።

ተንታኞች በመላ አገሪቱ በቅርቡ ምንነቱ ያልታወቀ ትኩሳት መከሰቱን ጨምሮ የተገለጸው ቁጥር እስካሁን ያልታየ ወረርሽኝ መከሰቱን የሚያመለክት ነው ብለዋል።

በአገሪቷ ያሉ 25 ሚሊየን ሕዝቦች በክትባት እጥረት እና ደካማ የጤና ሥርዓት ተጋላጭ መሆናቸውንም ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ሰሜን ኮሪያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቀረበላትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አስትራዜኒካ እና በቻይና የተመረተው ክትባት አልቀበልም ብላለች።

ይልቁንም ከአውሮፓውያኑ ጥር 2020 ጀምሮ ድንበሮቿን በመዝጋት ወረርሽኙን መቆጣጠር እንደቻለች ገልጻለች።

አገሪቷ በኮቪድ ወረርሽኝ ሲፈተኑ ከነበሩት ከደቡብ ኮሪያ እና ቻይና ጋር ትዋሰናለች።

ቻይና አሁን ላይ በትልልቅ ከተሞቿ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣል ኦሚክሮን ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እየታገለች ነው።

አርብ ዕለት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የጤና ተቋማትን መጎብኘታቸውን እና በመላ አገሪቷ የኮቪድ 19 ወረርሽን ሥርጭት መኖሩን መገንዘባቸውን ኬሲኤንኤ ዘግቧል።

ያለውን ሁኔታም "የህብረተሰብ ጤና ቀውስ" ብለውታል።

ሐሙስ ዕለት አዲስ የኮቪድ ሕጎችን ለማውጣት በተካሄደ ስብስባ ፕሬዚደንት ኪም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው በቴሌቪዥን ታይተዋል። ፕሬዚደንቱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው እንደሆነም ተነግሯል።

ፕሬዚደንት ኪም የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር የእንቅስቃሴ ገደብና በሥራ ቦታዎች መሰባሰብን ጨምሮ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ አዘዋል።

ይሁን እንጂ ወረርሽኙ መሠረታዊ ፍጆታዎች ወደ አገሪቷ እንዳይገቡ እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ። ይህም በአገሪቷ ያለውን የምግብ እጥረት እና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ሊያባብሰው ይችላል ተብሏል።

ደቡብ ኮሪያ ለጎረቤት አገሯ ሰብዓዊ እርዳታ እንደሰጠች የገለፀች ሲሆን ፒዮንግያንግ ግን ለዚህ ምላሽ አልሰጠችም።

ምንም እንኳን ደቡብ ኮሪያ ቀደም ብላ ወረርሽኙን በመቆጣጠር ረገድ ድል እየተቀዳጀች እንደሆነ ብትገልጽም በአገሪቷ የበሽታው ምልክቶችና ያልተረጋገጡ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች እንደነበሩ ተገልጿል።