ሪሃና የፌንቲ የውበት መጠበቂያ ምርቶቿን በአፍሪካ ልታቀርብ ነው

ታትሟል

ሪሃና ፌንቲ ቢውቲ እና ፌንቲ ስኪን የተባሉ የውበት መጠበቂያ ምርቶቿን ከዚህ ወር መጨረሻ ጀምሮ በስምንት የአፍሪካ ሃገራት ገበያዎች እንደሚቀርቡ አስታውቃለች።

ሪሃና በማህበራዊ ድረ-ገጿ ላይ እንዳሰፈረችው ምርቶቿን ወደ አህጉሪቷ የማምጣቱን ሁኔታ በጉጉት እየጠበቀች እንደነበር እና ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ተናግራለች።

የውበት ምርቶቹ በቦትስዋና፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ናሚቢያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ እንደሚገኙም ተጠቅሷል።

ሮቢን ሪሃና ፌንቲ ወይም ሪሃና ፌንቲ የተሰኘውን የውበት መጠበቂያ ምርቶቿን ከቅንጦት እቃዎች አምራቹ ሞየት ሄነሲ ሉዊ ቩቶን ጋር በመጣመር በአውሮፓውያኑ 2017 ጀመረች።

አርቲስቷ 1.7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት ያላት ሲሆን 1.4 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተው ከፌንቲ ቢውቲ የተገኘ ነው።

ኩባንያው በመጀመሪያዎቹ 40 ቀናት ውስጥ 100 ሚሊዮን ዶላር እንዳገኘ ተዘግቧል።

እንደ ፎርብስ ዘገባ ከሆነ እንደ ካይሊ ጄነር የውበት መጠበቂያ አምራች የሆነው ካይሊ ኮስሜቲክስ፣ የኪም ካርዳሺያን ኬኬደብልዩ ቢውቲና የጀሲካ አልባ ኦነስት ካምፓሊ በበለጠ የሪሃና የውበት ማስጠበቂያ ምርቶች ኩባንያ የበለጠ ገንዘብ ያገኛል።