ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማማለል ሞክራለች የሚል ዘገባ የወጣባት የምክር ቤት አባል እያነጋገረች ነው
የሌበር ፓርቲ አባልና ምክትል መሪ አንጄላ ራይነር የዩናይትድ ኪንግድም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን በእግሮቿ ለማማለል ሞክራለች የሚል ዜና መውጣቱን ተከትሎ ጉዳዩ በሰፊው መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
በምክር ቤት ውስጥ ከቦሪስ ጆንሰን ፊት ለፊት የምትቀመጠው የምክር ቤት አባል አንጄላ ራይነር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማማለል ትሞክራለች ሲል የጻፈው ሜይል ኦን ሰንደይ ጋዜጣ ነው፡፡
አንጄላ ራይነር ከቦሪስ ጆንሰን ፊት ለፊት በተቀመጠች ጊዜ አጭር ቀሚስ ለብሳ እግሮቿን አንድ ጊዜ በማነባበር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ገለጥ በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትኩረት ለመበተን ሞክራለች የሚል ዘገባ መውጣቱን ተከትሎ ጉዳዩ በታላቋ ብሪታኒያ ሰፊ መነጋሪያ የሆነው፡፡
ይህንን ዘገባ ያወጣው ሜይል ኦን ሰንደይ ጋዜጣ የአንጄላን ሁኔታ ‹ቤዚክ ኢንስቲንክት› (Basic Instinct) ከተሰኘው የሆሊውድ ዕውቅ ፊልም ጋር አዛምዶታል፡፡
‹ቤዚክ ኢንስቲንክት› እንደ አውሮጳዊያኑ በ1990ዎቹ መጀምርያ ለሕዝብ የቀረበ፣ ወሲባዊ ትዕይነቶችና ፈተናዎች የበዙበት ዝነኛ ፊልም ሲሆን ማይክል ዳግላስ የወንጀል መርማሪ ሆኖ በሻሮን ስቶን የተጋለጠ የእግር ውበት ተጠልፎ የሚወድቅበት ትዕይንት በይበልጥ ይታወሳል፡፡
የተከበረችው የምክር ቤት አባል አንጀላ ራይነር፣ ቦሪስ ጆንሰን ፊት ለፊት በመቀመጥ ተመሳሳይ የማማለል ሙከራ አድርጋለች ነው የሚለው ጋዜጣው፡፡
ዘገባውን አስደግፎ ያወጣው ከሻሮን ስቶን ፎቶ ጋር ሲሆን የምክር ቤት አባሏ ሆን ብላ ይህን የአማሎሽ ዘዴ እንደምትጠቀም ነገሩኝ ያለው ደግሞ በስም ሊጠራቸው ያልፈቀዳቸው የኮንዘርቫቲቭ ፓርቲ ተወካዮች ናቸው፡፡
የተከበረች የምክር ቤት አባል አንጄላ ራይነር ይህን ዘገባ "በኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ሴቶች ላይ የተቃጣ" ብለዋለች፡፡
አንጄላ ይህን በርሷ ላይ የተቃጣውን ዘገባ ክፉኛ ተችተዋለች፡፡ ሁኔታውም ‹ሴት ፖለቲከኞችን አሳንሶ የማየትና የማሸማቀቅ ሙከራ› ስትል ገልጻዋለች፡፡
ይህን ዘገባ ተከትሎ በርካታ የምክር ቤት አባላትና ሌሎች ስመ ጥር ፖለቲከኞች ለአንጄላ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዘገባውን ያወጣውን ሜይል ኦን ሰንደይ ጋዜጣም ከፍተኛ ውግዘት ደርሶበታል፡፡
የኮንዘርቫቲቭ አባል ካሮላይን ኖክስ በርካታ ሴት የምክር ቤት አባላት እንዲህ ዓይነት አስቀያሚ ዘገባዎች ይከተሏቸዋል ሲሉ ዘገባውን አውግዘዋል፡፡
የቀድሞዋ ሚኒስትር አንድሪያ ሊድሰም ደግሞ በትዊተር ገጻቸው ‹‹በዚህ ዘገባ አዝኛለሁ፤ ተቀባይነት የሌለውና አሳፋሪ› ሲሉ ተችተውታል፡፡
ይህን በወ/ት አንጀላ ላይ የተሠራውን ዘገባ ቦሪስ ጆንሰንም አውግዘውታል፡፡‹‹በብዙ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከአንጄላ ራይነር ጋር የማንስማማ ቢሆንም በሷ ላይ በተጻፈው ነገር አዝኛለሁ፡፡ ይህ ሴቶችን የመናቅና የማንቋሸሽ ጉዳይ እንጂ ሌላ አይደለም›› ብለዋል፡፡
የሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ኪየር ሰታርመር ዘገባውን አውግዘዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ምንጮች ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ቦሪስ ጆንሰንም ቢሆን በግላቸው አንጀላ ራይነርን በስልክ የጽሑፍ መልእክት ‹አይዞን› ሲሉ አጽናንተዋል፡፡
ዘገባው ጨምሮ የምክር ቤት አባሏ ይህን የማማለል ስልት ምንጊዜም ቦሪስ ጆንሰን ጥያቄዎች ሲገጥሟቸው ምክር ቤት ውስጥ ከፊት ለፊታቸው በመቀመጥ ከመንገዳቸው ልታስታቸው ትሞክራለች ሲል ጽፏል፡፡