በአፍጋኒስታን መስጊድ ውስጥ ትናንት አርብ በተፈጸመ ጥቃት 33 ሰዎች ተገደሉ

መስጊድ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ጥቃቱ በከተማዋ ምሥራቃዊ ከተማ የሱፊ መስጊድ ላይ ሲፈጸም ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ታትሟል

በአፍጋኒስታን ኩንዱዝ በተሰኘችው ከተማ በሚገኝ የሱኒ መስጊድ ላይ በተሰነዘረ የቦንብ ጥቃት 33 ሰዎች ሲገደሉ ህጻናትን ጨምሮ 43 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ጥቃቱ በከተማዋ ምሥራቃዊ ከተማ የሱፊ መስጊድ ላይ ሲፈጸም ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ጥቃት አንድ ቀን ቀደም ብሎ በአፍጋኒስታን አራት የተለያዩ ከተሞች ላይ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን ለሁሉም ጥቃት አይኤስ ኃላፊነትቱን ወስዷል።

የታሊባን አስተዳደር እስላማዊ ታጣቂውን አይኤስ ቢያሸንፈውም፥ ቡድኑ ለአፍጋኒስታን አዲስ መሪዎች ትልቅ የደህንነት ፈተና እንደሆነ አስታውቋል።

ትላንት በጁመአ ጸሎት ላይ በኩንዱዝ የተፈጸመውን ጥቃት ፈጽሜያለው ብሎ ኃላፊነት የወሰደ ቡድን እስካሁን አልተገኝም።

በመስጊዱ አቅራቢያ የሚሰራ አንድ ነጋዴ ክስተቱ እጅግ አሰቃቂ እንደነበር ለኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግሯል።

ለጥቃቱ ጥቅም ላይ የዋለው ቦንብ እና ፍንዳታው ሐሙስ ዕለት በማዛሪ ሻሪፍ በሺያ ሙስሊም መስጊድ ላይ ከተፈጸመው እና ቢያንስ 31 ሰዎች ከሞቱበት እና 87 ሰዎች ከተጎዱበት ጋር ተመሳሳይነት አለው ተብሏል።

በተመሳሳይ ቀን በኩንዱዝ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ደግሞ አራት ሰዎች ተገድለው 18 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

ሁለቱን ጥቃቶች ስለመፈጸሙ ያረጋገጠው አይኤስ፥ ጥቃቶቹ በቅርቡ የተገደለውን የቡድኑን መሪ እና ቃል አቀባይ ደም ለመመለስ' "ብቀላ" በሚል ስያሜ የተጀመረው ዓለም አቀፍ ዘመቻ አካል ነው ብሏል።

የአሜሪካና የአጋሮቿ ጦር ከአፍጋኒስታን ከወጣ በኋላ በሀገሪቱ ከ20 ዓመታት በኋላ የቦንብ ጥቃቶች ትርጉም ባለው ደረጃ እየቀነሱ ነው።

አይኤስ በአፍጋኒስታን ውስጥ የትኛውንም አካባቢ የማይቆጣጠር ቢሆንም ታሊባን ስልጣን ከያዘ በኋላ ግን ከዚህ በፊት ፈጽሞ ተንቀሳቅሰው በማያውቁባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ እንደሆነ ይገለጻል።

የሱፊ እስልምና አፍጋኒስታን በምትገኝበት ቀጠና ለምዕተ ዓመታት የተተገበረ ነው። አብዛኞቹ ጽንፈኛ ሱኒዎች የሱፊ እና ሺያ ሙስሊሞችን እንደ "መናፍቅ" ይቆጥሯቸዋል።

የታሊባኑ ቃል አቀባይ ጥቃቱን ሰይጣናዊ ድርጊት ነው ያሉ ሲሆን ጥቃት አድራሾቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና ለመቅጣት ብርቱ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በአፍጋኒስታን የተመድ ምክትል ተጠሪ ራምዚ አላካባሮቭ በዚህ ሳምንት የተፈጸሙ ጥቃቶች የአፍጋኒስታን ህዝብ በየቀኑ የሚጋፈጠው መራር የሆነ የደህንነት ስጋት እና አደጋ የሚያስታውስ ነው ብለዋል።

ጥቃቶቹ በሳምን ውስጥ መቶ ንጹሃንን ተጎጂ ማድረጋቸውን ያስታወሱት ተጠሪዋ ድርጊቱ ተቀባይነት የሌለው እና በፍጥነት ሊቆም የሚገባው ነው ብለዋል።