ሁለት ሺህ የሚሆኑ የኬንያ ፖሊሶች ሥራቸውን ለመስራት በአዕምሮ ብቁ አይደሉም ተባለ

የኬንያ ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ወደ 2000 የሚጠጉ የኬንያ ፖሊስ መኮንኖች መደበኛ ሥራቸውን ለመከወን በአዕምሮ ብቁ እንዳልሆኑ የብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት ኃላፊ ተናገሩ።

ኃላፊው ኢንስፔክተር ጀነራል ሂላር ሙትያምባይ ማክሰኞ ዕለት በተካሄደው የጳጳሳትና እና ቀሳውስት ፎረም ላይ እንዳሉት ሁሉም የፖሊስ መኮንኖች የሕክምና ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ በአስደንጋጭ ሁኔታ የአዕምሮ ጤና ችግር የገጠማቸው በርካታ ፖሊሶች ተገኝተዋል።

ይህ ይፋ የሆነው በፖሊስ ኃይሉ ውስጥ ለድብርት የሚጋለጡ እና ራሳቸውን የሚያጠፉ ፖሊሶች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ነው።

ኬንያ በብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት ሥር የሚሰሩ 100 ሺህ የፖሊስ መኮንኖች አሏት።

የብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት ኃላፊው ሙትያምባይ የአዕምሮ ጤና ችግር የገጠማቸውን የፖሊስ መኮንኖች ከሥራ የማሰናበት ሒደት መጀመሩን ገልጸው " የአዕምሮ ጤና ችግር ያለበት ፖሊስ መኖሩ ምንም ጠቀሜታ የለውም" ብለዋል።

" የሥራ መሳሪያችን ሽጉጥ ነው፤ ከዚያ በስህተት አንድ ጥይት ከወጣ መዘዙ ብዙ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ይሁን እንጂ ባለው አሰራር መሠረት የፖሊስ መኮንኖቹን ከሥራ የማሰናበት ሒደቱ ቀላል እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የፖሊስ መኮንኖች የአዕምሮ ጤና ሁኔታ በአገሪቷ አስጊ እየሆነ የመጣ ሲሆን መንግሥት ችግሩን ለመፍታት እየሰራ ነው።

አሁን ላይ ፖሊስ የአዕምሮ ጤና አገልግሎቶችን ለመስጠት በጤና ሚኒስቴር የተደገፈ የስነ ልቦና አማካሪዎችን እና የአዕምሮ ሐኪሞችን ያካተተ የራሱ የሆነ የጤና ቦርድ እንዳለውም ሙትያምቢ ተናግረዋል።