ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በስዊድን አንድ ትምህር ቤት ውስጥ በተከሰተ ሁከት ሁለት ሴቶች ተገደሉ
በስዊድኗ ማልም ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ በተፈጠረ ሁከት በ50ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁለት ሴቶች መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
የትምህርት ቤቱ ተማሪ የሆነ የ18 ዓመት ወጣት በሴቶቹ ግድያ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል።
ፖሊስ ሁለቱ ሴቶች በምን አይነት ጥቃት እንደተገደሉ ያለው ነበር የለም። ይሁን እንጂ ፖሊስ የተተኮሰ ጦር መሳሪያ አለመኖሩንም አስታውቋል።
የስዊድን መገናኛ ብዙሃን ግን በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው የ18 ዓመት ወጣት፤ ቢላዋ እና መጥረቢያ ይዞ እንደነበር እየዘገቡ ነው።
ይህ ወጣት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ጋር ስልክ ደውሎ ወንጀሉን መፈጸሙን ተናግሯል ሲሉ ጨምረው ዘግበዋል።
ሁከቱ ሲያጋጥም ተማሪዎች እና መምህራንን ጨምሮ ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎች በትምህርት ቤቱ ነበሩ። ጉዳት የደረሰባቸው ሁለቱ ሴቶች በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም ሕይወታቸው ሊተርፍ አልቻለም።
የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ፔትራ ስቴንኩላ የሁለቱን ሴቶች መገደል አረጋግጠው ለወዳጅ ዘመድ መጽናናትን እንመኛለን ብለዋል።
ፖሊስ በትምህርት ቤቱን ቅጥር ጊቢ ፍተሻ ማድረጉን እና ሌሎች የወንጀሉ ተባባሪ የሆኑ ሰዎች ስለመኖራቸው ምንም አይነት ማረጋገጫ አልተገኘም ብሏል።
መምህራን እና ተማሪዎች ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ፖሊስ ወደ ትምህር ቤቱ ቅጥር ገብቶ በክፍሎቻቸው ውስጥ ሳይንቀሳቀሱ ለሰዓታት እንዲቀመጡ እንዳዘዛቸው ገልጸዋል።
ፖሊስ የጥቃቱ ምክንያት ምንድነው የሚለውን እያጣራ መሆኑን ገልጿል።
"ምን እንደተፈጠረ እና ይህ አስከፊ ጥቃት ለማድረስ ምክንያት የሆነውን የማጥራት ትልቅ ሥራ ይጠብቀናል" ብለዋል የሰሜን ማልም ፖሊስ አዛዥ አሳ ኒልሰን።