ለሁለት ዓመት ድንበሯን ዘግታ የቆየችው ኒው ዚላንድ በሯን ልትከፍት ነው

ታትሟል

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከሁለት ዓመታት በላይ ድንበሯን ዘግታ የቆየችው ኒው ዚላንድ በስተመጨረሻ በሮቿን ልትከፍት እንደሆነ ይፋ አድርጋለች።

ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ አውስትራሊያዊያን ምንም ዓይነት በለይቶ ማቆያ መቆየት ሳያስፈልጋቸው በነፃነት መግባት ይችላሉ።

ከ60 ሃገራት የሚመጡ ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሰዎች ደግሞ ከግንቦት ወር ጀምሮ መግባት እንዲችሉ ይፈቀድላቸዋል።

ከእነዚህ ሃገራት መካከል ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይት ኪንግደም ይገኙበታል።

ሁሉም ወደ ኒው ዚላንድ የሚመጡ ተጓዦች ከኮቭድ ነፃ መሆናቸውን የሚያሳይ ወረቀት ማሳየት አለባቸው።

ኒው ዚላንድ ድንበሯን ሙሉ በሙሉ ዝግ በፈረንጆቹ መጋቢት 2020 ነበር።

ኒው ዚላንድ ለአውስትራሊያ ከሰጠችው ለአጭር ጊዜ የቆየ የጉዞ ፈቃድ ውጭ ድንበሯን ለማንም ሳትከፍት ቆይታለች።

አሁን ላይ ወደ ሃገሪቱ መግባትና መውጣት የሚችሉት የኒው ዚላንድ ዜጎች ብቻ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደን እንዳሉት ኒው ዚላንድ "ዓለምን ለመቀበል ዝግጁ ናት።"

"አሁን በተሰጠን መመሪያ መሠረት ድንብራችንን ለመክፈት ሁሉም ነገር ምቹ ይመስላል። ቱሪስቶቻችንም ይመለሳሉ" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሯ።

ወደ ኒው ዚላንድ ለመግባት ቪዛ ቀድሞ ያላቸው ሰዎች ከግንቦት ወር ጀምሮ እንደልባቸው መንቀሳቀስ ይችላሉ።

ኒው ዚላንድ ጠንካራ የሚባል የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣሏ የኮቪድ-19 ስርጭትን በመቆጣጠር ስሟ በተደጋጋሚ ይነሳል።

ከኒው ዚላንድ ነዋሪዎች 95 በመቶው ተከትበዋል። ወረርሽኙ ከጀመረ ወዲህ በኮቪድ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 115 ብቻ ነው።

ያልተከተቡ ሰዎች ሥራ አያገኙም መባሉን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ዌሊንግተን ተቃውሞ ተቀስቅሶ እንደነበር አይዘነጋም።

ምንም እንኳ ኒው ዚላንድ ድንበሯን ከፍታ፤ እጇን ዘርግታ እንግዶች ለመቀበል ብትዘጋጅም አሁንም ቢሆን በርከት ብሎ መሰባሰብም ሆነ ያለጭንብል መንቀሳቀስ ክልክል ነው።