የሜክሲኮ ፍርድ ቤት ጽንስ ማቋረጥን ሕጋዊ አደረገ

ሜክሲኮ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የሜክሲኮ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጽንስ የማቋረጥ ተግባርን እንደ ወንጀል መቁጠር ሕገ-መንግስታዊ አይደለም ሲል ወሰነ።

በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው የኩዋሃላ ግዛት የተሰጠው ይህ ውሳኔ፤ ጽንስ የሚያቋርጡ ሴቶች በወንጀል እንዳይከሰሱ ያደርጋል።

በሜክሲኮ ከአራት ግዛቶች በስተቀር በሁሉም የአገሪቱ ግዛቶች ጽንስ ማቋረጥ የተከለከለ ተግባር ሆኖ ቆይቷል። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ሉዊስ ማሪያ አጉሊያር ውሳኔውን "ለሴቶች መብት ታሪካዊ እርምጃ" በማለት ገልፀውታል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትላንት ማክሰኞ ነበር ኮዋሁሊላ ግዛት ጽንስ ማቋረጥን ከወንጀል ዝርዝሮቹ ውስጥ እንዲያወጣ የወሰነው። ይህ ገዢ ውሳኔ በመላ ሜክሲኮ ፅንስ ማቋረጥ ከወንጀል ዝርዝር ውስጥ እንዲወጣ በር ከፋች ሆኗል።

በአስገድዶ መድፈር የተፈጠረ እርግዝና አልያም ጸንሱ የእናትየውን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲኖር እንጂ በበርካታ የሜክሲኮ ግዛቶች ውስጥ ጽንስ ማቋረጥ ወንጀል ነው።

በሜክሲኮ የፍትሕ ስርዓት ውስጥ የሚሰሩ አንድ ምንጭ እንዳሉት ውሳኔው በመላው ሜክሲኮ ተፈጻሚነት ይኖረዋል። እንዲሁም ጽንስ ማቋረጥ ወንጀል በሆነባቸው ግዛቶች ውስጥ በሂደት ላይ ያሉ የጽንስ ማቋረጥ የክስ ሂደቶችም እንዲቋረጡ የሚያደርግ ነው።

የጽንስ ማቋረጥ መብት ላይ ዘመቻ ሲያካሂድ የቆየው ጂአይአርኢ የተሰኘው ቡድን ውሳኔውን "ታሪካዊ" በማለት ገልጾታል።

"በመላ ሜክሲኮ ሴቶች እና ልጅ የመውለድ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ይህንን ልጅ የማግኘት እጣፈንታቸውን በነጻነት እንዲወስኑ ያስችላል ብለን እናምናለን" ሲል ተቐሙ ገልጿል።

ውሳኔው የተሰጠባት ግዛት ከአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ጋር ትዋሰናለች።

የቴክሳስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከስድስት ሳምንታት በላይ የቆየ ጽንስን ማቋረጥን የሚከለክል ሕግ ማጽደቁ ይታወሳል። ታዲያ ይህ በሜክሲኮ የተሰጠው ውሳኔ ከቴክሳስ የሚመጡ እና ሕጋዊ ጽንስ ማቋረጥን ለሚፈልጉ ሰዎች መንገዶችን ሊከፍት ይችላል ተብሏል።