ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታሊባን በኤፍቢአይ የሚፈለገውን ግለሰብ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር አድርጎ ሾመ
በቅርቡ የአፍጋኒስታን መንግሥትን ከስልጣን አባሮ አፍጋኒስታንን የተቆጣጠረው ታሊባን ጊዜያዊ መንግሥት ይፋ አድርጓል።
በዚህ መሠረት ታሊባን ከመሪዎቹ መካከል አንዱን መሪ አድርጎ የመረጠ ሲሆን በአሜሪካው የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) የሚፈለገውን ግለሰብ ደግሞ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር አድርጎ ሾሟል።
ከታሊባን መስራቾች አንዱ ሙላህ ሞሐመድ ሐሰን አከሁንድ ታሊባን የቋቋመውን መንግሥት የሚመሩ ይሆናል። ሌላኛው የታሊባን መስራች ሙላህ አብዱል ጋጅኒ ባርዳር ደግሞ ምክትል ይሆናሉ ሲሉ የታሊባን ቃል አቀባይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሳራጁዲን ሃቃኒ ደግሞ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው ተሹመዋል። ሳራጁዲን ሃቃኒ የሚባሉት ግለሰብ "ሃቃኒ ኔትዎርክ" ተብሎ የሚጠራው የታጣቂ ቡድን መሪ ናቸው።
ሃናቂ ኔትዎርክ አሸባሪ ድርጅት ተብሎ በአሜሪካ መንግሥት የተፈረጀ ድርጅት ነው።
"የአገራችን ሕዝብ አዲስ መንግሥት እንዲመሰረት እየተጠባበቁ እንደሆነ እናውቃለን" ሲሉ የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ተናግረዋል።
ታሊባን አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል ከሦስት ሳምንት በፊት መቆጣጠሩ ይታወሳል።
ሌሎች በታሊባን መንግሥት ውስጥ ቦታ የሚኖራቸው ሙላህ ያቆብ ተጠባባቂ መከላከያ ሚንስትር እንዲሁም ሳላም ሃናፊ ምክትል ሚንስትር ሆነው ተሹመዋል።
ታሊባን የሽግግር መንግሥቱን ባስተዋወቀበት ወቅት አፍጋኒስታንን "እስላማዊ ግዛት" ሲል አውጇል።
የአዲሱ ካቢኔ አባላት ባጠቃላይ ወንዶች ናቸው። ከዚህ ቀደም የአስተዳደር መዋቅሩ አካታች እንደሚሆን ቢናገሩም እስካሁን የተመረጡት ወንዶች ናቸው።
አዲሱ አስተዳደር የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ማስተካከልን ጨምሮ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘትና ሌሎችም ብዙ ፈተናዎች ይጠብቁታል።
የታሊባን ከፍተኛ መሪ ማዋሊ ሂባቱላህ አኩንዳዝዳ አስተዳደሩ ሸሪዓን እንዲተገብር ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ታሊባን ከጎረቤት አገሮች ጋር "ጠንካራ እና ጤናማ ግንኙነት ይፈልጋል" ሲሉም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በመግለጫቸው ታሊባን "ከእስላማዊ ሕግ እና ከአገሪቱ ብሔራዊ መርህ ጋር የማይቃረኑ" ዓለም አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶችን እንደሚያከብርም አክለዋል።
ታሊባን ሥልጣን ከያዘ ወዲህ መሪው በአደባባይ ሲናገሩ የመጀመሪያው ነው።
ለመሆኑ ታሊባኖች እነማን ናቸው?
ታሊባን ማለት በፓሽቶ ቋንቋ "ተማሪዎቹ" ማለት ነው። ፓሽቶ በፓኪስታን፣ አፍጋኒስታንና ኢራን ውስጥ የሚነገር ቋንቋ ነው።
ታሊባን በጎርጎሮሲያዊያኑ 1990ዎቹ መጀመርያ በሰሜን ፓኪስታን ብቅ ያለ መደበኛ ያልነበረ እንቅስቃሴ ሲሆን ይህም የያኔዋ ሶቭየት ኅብረት ከአፍጋኒስታን ጦሯን ማስወጣቷን ተከትሎ የተጀመረ ነበር።
ከሳኡዲ አረቢያ ጥብቅ እስልምናን በሚሰብኩ ሰዎች የተማረኩ ወጣቶች አማካኝነት ስብስቡ እየተጠናከረ መጣ።
መንፈሳዊ እንቅስቃሴው ፖለቲካዊ መልክን እየያዘ መጣ። ከኢመደበኛ እንቅስቃቄ ወደ ቡድን ከፍ አለ።
ታሊባኖች በተለይም ሙስናን በማጥፋትና ሥርዓት አልበኝነትን በመቀልበስ ስማቸው ይወደሳል።
የታሊባን ስም ወደ ትልቅ አጀንዳነት የተቀየረው ከመስከረም 11ዱ የሽብር ጥቃት ወዲህ ነው።
ታሊባን የኒው ዮርክ መንትዬዎቹን ሕንጻዎች ጥቃት ላደረሰው የአል-ቃኢዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ከለላ በመስጠቱ ሁኔታዎች መልካቸውን ሊቀየሩ ቻሉ።
በጥቅምት 7፣ 2001 የአሜሪካ መራሹ ጦር በአፍጋኒሰታን ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመረ።
በታኅሣሥ የመጀመርያው ሳምንት 2001 ዓ.ም የታሊባን አስተዳደር በይፋ ፈራረሰ።
ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላም በአፍጋኒስታን የነበሩት የአሜሪካ ወታደሮች አፍጋኒሰታንን መልቀቃቸውን ተከትሎ ታሊባን አፍጋኒስታንን መቆጣጠር ችሏል።