ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር በቅስቀሳ ላይ ሳሉ በድንጋይ ተመቱ
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉት ወቅት በተወረወረባቸው ድንጋይ እንደተመቱ ተገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ የቢራ ፋብሪካ ጎብኝተው ወደ መኪናቸው በመመለስ ላይ ሳሉ ነው በአነስተኛ ድንጋዮች ጥቃት የተፈጸመባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳት አልደረሰባቸውም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ከተያዘለት ቀን በፊት በያዝነው ወር አጋማሽ ላይ የአብዛኛውን የመንግሥት ስልጣን በእጃቸው ለማስገባት በማሰብ ምርጫ እንዲደረግ ጠርተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ለዚህ ምርጫ ቅስቀሳ ላይ ሳሉ ነው ድንጋይ የተወረወረባቸው።
ትሩዶ የኮቪድ-19 ክትባት አሰጣጥና ክልከላዎችን በተመለከተ ከፍተኛ ተቃውሞዎች እየገጠማቸው በመሆኑ የምርጫ ቅስቀሳቸውን እንዳሰቡት መምራት አልቻሉም።
ከአንድ ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ሲሰናዱ የተቆጡ ተቃዋሚዎች ስነስርዓቱን በመረበሻቸው ምክንያት ቅስቀሳውን ለመሰረዝ ተገደዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንጋይ ከተወረወረባቸው በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ምናልበት ትከሻቸው ላይ ሳይመቱ እንዳልቀሩ ገልጸዋል። ሁኔታውንም በአውሮፓውያኑ 2016 አንዲት ሴት የዱባ ፍሬ ከወረወረችባቸው አጋጣሚ ጋር አመሳስለውታል።
የካናዳው 'ሲቲቪ ናሽናል ኒውስ' ዘጋቢ የሆነ አንድ ጋዜጠኛ ደግሞ የተወረወሩ ድንጋዮች በአካባቢው የነበረ የመገናኛ ብዙሀን የሚጠቀሙት ባስ ላይ ማረፋቸውን ገልጿል። ነገር ግን ማንም ሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም ተብሏል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ኤሪን ኦቶሌ ደግሞ ሁኔታውን በመቃወም አጸያፊ ተግባር ሲሉ ገልጸውታል።
"ፖለቲካዊ አመጽ መቼም ቢሆን ተቀባይነት የለውም። መገናኛ ብዙሃንም ቢሆኑ ከማንኛውም አይነት ማስፈራራት እና ጥቃት ነጻ መሆን አለባቸው" ብለዋል በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የፊታችን መስከረም ከሚካሄደው ምርጫ በፊት የኮቪድ-19 ክትባት ጉዳይ ቅድሚያ እንዲሰጠው ይፈልጋሉ።
ባለፈው ወር መንግሥት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በፌደራል የሚተዳደሩ ዘርፎችን ጨምሮ ሁሉም የሲቪል አገልጋዮች በፈርነጆቹ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ መከተብ አለባቸው። አለበለዚያ ስራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉም ተነግሯቸዋል።
የንግድ አውሮፕላን፣ መርከብ እና የባቡር ተሳፋሪዎችም ቢሆኑ ከመጓዛቸው በፊት ቅድሚያ ክትባቱን መውሰድ እንዳለባቸው ተገልጿል።
ካናዳ እስካሁን ድረስ በዓለማችን በርካታ ዜጎችን ከከተቡ አገራት መካከል ትጠቀሳለች።