ኮቪድ ያሰራጨው የቬትናም ዜጋ አምስት ዓመት ተፈረደበት

ሊ ቫን ትሪ

የፎቶው ባለመብት, THANH NIEN

ታትሟል

አንድ ቬትናማዊ ግለሰብ የኮቪድ-19 መመሪያዎችን በመጣስ እና ቫይረሱን በማሰራጨት ወንጀል ተከስሶ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የአምስት ዓመት እስር ተፈረደበት።

ሊ ቫን ትሪ አደገኛ እና ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ የሚተላለፍ በሽታን በስምንት ሰዎች ላይ በማሰራጨት ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን ተከትሎ ነው ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈበት።

ግለሰቡ ኮቪድ ካስያዛቸው ሰዎች መካከል አንድ ግለሰብ ህይወቱ አልፏል ተብሏል።

እስከ ቅርብ ጊዜያወት ድረስ ቬትናም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በመቆጣጠርና ጥብቅ መሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማ አገር ነበረች።

ነገር ግን ከባለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ አዲሱ ዴልታ የተሰኘው የቫይረሱ ዝርያ በአገሪቱ መከሰቱን ተከትሎ በርካቶች በቫይረሱ እየተያዙ ነው።

እስካሁን ድረስም በቬትናም ከ530 በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 13ሺህ 300 ሰዎቸው ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል። ነገር ግን ከዚህ ቁጥር አብዛኛው የተመዘበው ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ መሆኑ ነገሮች ምን ያክል አሳሳቢ ስለመሆናቸው ማሳያ ነው ተብሏል።

በስርጭት ደረጃ ደግሞ ሆ ቺ ሚኒ ከተማ ውስጥ በርካቶች በቫይረሱ ተይዘዋል።

በሰኔ ወር መጀመሪያ አካባቢ ጥፋተኛ የተባለው የ28 ዓመቱ ሊ ከሆ ቺ ሚኒ ከተማ ተነስቶ ወደ ትውልድ አካባቢው ካ ማው ግዛት በሞተር ሳይክል ተጉዟል።

ካ ማው ከደረሰ በኋላ ደግሞ ስለ ጉዞ ታሪኩ እና ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ለተጠየቀው ጥያቄ ሀሰተኛ መረጃ ሰጥቷል፤ በተጨማሪም እራሱን መለየት ሲገባው ይህንን መመሪያ ተግባራዊ አላደረገም።

የአካባቢው ባለስልጣናት ከወራት በፊት እንዳስታወቁት ማንኛውም ተጓዥ ወደ ካ ማው ግዛት ሲገባ እራሱን ለ21 ቀናት ላይቶ ማቆየት ግዴታ ነው።

ከትንሽ ቆይታ በኋላ ሊ የኮቪድ19 ምርመራ ሲደረግለት በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠ ሲሆን በወቅቱም ቫይረሱን ለቤተሰቡ አባላት እንዲሁም ለህክምና የሄደበት የጤና ማዕከል ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎችን አስይዟል።

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤትም ግራ ቀኙን ከሰማ በኋላ ሊ አምስት ዓመት እስራት እና 880 ዶላር መቀጮ ፈርዶበታል።