ከእስር የተለቀቀው የጋዳፊ ልጅ ቱርክ ገባ

ታትሟል

ሦስተኛው የጋዳፊ ልጅ ከሊቢያ እስር ቤት ከተለቀቀ በኋላ ወደ ቱርክ፣ ኢስታንቡል ማምራቱ ተዘገበ።

ሰዒድ ጋዳፊ የወላጅ አባቱ ሞዓመር ጋዳፊ ግድያን ተከትሎ በስደት ከሸሸባት ኒጀር ለሊቢያ ተላልፎ ተሰጥቶ ከእአአ 2014 ጀምሮ በእስር ላይ ቆይቶ ነበር።

ሰዒድ የሊቢያ ልዩ ኃይሎች አዛዥ ሳለ ግድያን ጭምሮ በርካታ ወንጀሎችን ፈጽሟል የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር። ይሁን እንጂ እአአ 2018 ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር ሰዒድ በቀረቡበት ክሶች ጥፋተኛ አይደለም ብሎት ነበር።

ሰዓዲ ከእስር የተለቀቀው ከፍተኛ የብሔር መሪዎች እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አብዱልሃሚድ ዴኢቤህ ድርድር ካደረጉ በኋላ መሆኑን ሮይተርስ የዜና ወኪል የሊቢያ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።

ሦስተኛው የጋዳፊ ልጅ ከእስር ቤት እንደወጣ የግል አውሮፕላን ተሳፍሮ ወደ ኢስታንቡል ገብቷል ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለው የሊቢያ መንግሥት የሰዒድ ከእስር መለቀቅ ብሔራዊ እርቅ እንዲመጣ አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚል ተስፋ አለኝ ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጋዳፊ ሁለተኛ ልጅ የሆነው ሰይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ ከሳምንታት በፊት የእስር ትዕዛዝ ወጥቶበታል።

በሙዓመር ጋዳፊ የሥልጣን ዘመን ከፍተኛ ሥልጣን ከነበረው የሩሲያ ቅጥረኛ ቡድን ጋር ግንኙነት አለው በሚል ምክንያት ነው የእስር ትዕዛዝ የወጣበት።

በሰለንድ ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የተማረው ሰይፍ አል-ኢስላም ከአባቱ መንበረ ሥልጣኑን ይረከባል ተብሎ የሚጠበቅ ነበር።

ይሁን እንጂ ሕዝባዊ አብዮቱን ተከትሎ የጋዳፊ መንግሥት ከተበተነ በኋላ ሰይፍ አል-ኢስላም በአማጺ ቡድን እአአ 2011 ተይዞ ዚንታና ወደተባለች ከተማ ተወስዶ ለስድስት ዓመታት በእስር ቆይቶ ነበር።

ሰይፍ በአማጺ ቡድኑ ቁጥጥር ሥር ሳለ ትሪፖሊ ባለ ፍርድ ቤት በተቃዋሚዎች ላይ ለደረሰው ግድያ ጥፋተኛ ተብሎ የሞት ፍርድ ተላልፎበት ነበር።

ሰይፍ አል-ኢስላም በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዓለም አቀፉ የወንጀሎች ፍርድ ቤትም ይፈለጋል።

በአማጺያን ቁጥጥር ሥር ለስድስት ዓመታት የቆየው ሰይፍ ከጥቂት ወራት በፊት ከኒው ዮርክ ታይምስ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ቀጣይ በሊቢያ በሚደረገው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ የመወዳደር እቅድ እንዳለው ተናግሮ ነበር።