ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሊዮኔል ሜሲ መዳረሻው የት ይሆን?
የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ባጋጠመው የገንዘብ እና የአሠራር ችግሮች ምክንያት ሊዮኔል ሜሲ ከክለቡ ጋር እንደማይቆይ አስታውቋል።
የ34 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ ከባለፈው ወር ጀምሮ ከባርሴሎና ጋር የነበረው ኮንትራት መጠናቀቁን ተከትሎ የማንም ክለብ ተጫዋች ሳይሆን ቆይቷል።
ምንም እንኳን ባለፈው ወር አጋማሽ ላይ ደሞዙን በግማሽ ቀንሶ በባርሴሎና ለመቆየት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ክለቡ ቢያንስ ሦስት ተጫዋቾችን መሸጥ ነበረበት። ነገር ግን ባርሴሎና እሸጣቸዋለው ብሎ ያሰባቸውን ተጫዋቾችን መሸጥ ሳይችል ቀርቷል።
"የተጫዋቹም ሆነ የክለቡ ፍላጎቶች አለመሟላታቸው ሁለታችንንም አሳዝኖናል'' ብሏል ባርሴሎና ባወጣው መግለጫ።
ባርሴሎና ሊዮኔል ሜሲ ከክለቡ ጋር የነበረውን ለ21 ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት ትናንት ሐሙስ ዕለት አዲስ ኮንትራት በመፈረም ለተጨማሪ ዓመታት እንደሚያራዝም ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም በላ ሊጋ ችግር ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል ብሏል።
ሜሲ በመርህ ደረጃ እስከ አውሮፓውያኑ 2026 ድረስ የሚያቆየው አዲስ ስምምነት ላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን ላ ሊጋ ደግሞ ባርሴሎና ሜሲንም ሆነ ሌሎች አዳዲስ ተጫዋቾችን ከመመዝገቡ በፊት ወጪውን መቀነስ አለበት ብሏል።
"ምንም እንኳን ባርሴሎና እና ሊዮኔል ሜሲ አዲስ ኮንትራት ለመፈራረም ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ባለው የፋይናንሻል እና የአሠራር ችግሮች ምክንያት ሊሳካ አልቻለም'' ብሏል ባርሴሎና ባወጣው መግለጫ።
"የባርሴሎና እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቹ በነበረባቸው ዓመታት ለክለቡ ላደረገው አስተዋጽኦ በሙሉ ምስጋና ወደፊት ለሚጠብቀው የእግር ኳስም ሆነ የግል ሕይወቱ መልካሙን ሁሉ እንመኝለታለን።''
ሊዮኔል ሜሲ በባርሴሎና ቆይታው 672 ኳሶችን ከመረብ በማገናኘት የክለቡ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን ከቡድኑ ጋር 10 የላ ሊጋ ዋንጫዎችን፣ አራት የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫዎችን፣ ሰባት ኮፓ ዴላሬ ዋንጫወዎችን ማሸነፍ ችሏል።
እንዲሁም ስድስት ጊዜ የባሎንዶር ሽልማትን ማግኘት የቻለ ታላቅ ተጫዋች ነው።
ሜሲ በባርሴሎና እንደማይቀጥል መረጋገጡን ተከትሎ በሚቀጥሉት ሳምንታት በርካታ የዓለማችን ክለቦች ተጫዋቹን የግላቸው ለማድረግ እንደሚጥሩ ይጠበቃል።
የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ እና የፈረንሳዩ ፒኤስጂ ደግሞ ቀንደኛ ፈላጊዎቹ እንደሆኑ ይታመናል።
ሜሲ ወደ ማንቸስተር ሲቲ የሚያቀና ከሆነ በርካታ ዋንጫዎችን አብሮት ካነሳውና ከቀድሞው የባርሴሎና አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ጋር በድጋሚ የመጫወት እድል ያገኛል።
ሜሲ ወደ አሜሪካ የመሄድ ፍላጎት እንዳለው አልደበቀም። ባለቤቱ አንቶኔላ ከቀድሞው የክለብ ጓደኛው ሴስክ ፋብሬጋስ ባለቤት ጋር ጥብቅ የሆነ ወዳጅነት መስርታለች።
ፋብሬጋስ እና ባለቤቱ ደግሞ ሜሲና ባለቤቱ ወደ አሜሪካ መጥተው የመጨረሻዎቹን የእግር ኳስ ዓመታት እዚያ እንዲያሳልፉ ይፈልጋሉ።
ሊዮኔል ሜሲ ባርሴሎናን የተቀላቀለው የ12 ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር። ከነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ግን የ33 ዓመቱ ሜሲ ጫማውን የሚሰቅለው በየትኛው ክለብ ነው የሚለውን መወሰን ይጠበቅበታል።
ከወራት በፊት ደግሞ የፒኤስጂው ኮከብና የቀድሞ የባርሴሎና ተጫዋች ኔይማርም በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሰጥቷል።
ባለፈው የፈረንጆቹ ታኅሣስ ላይ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድን ካሸነፉ በኋላ ኔይማር "ከዚህ በኋላ ከምንም በላይ የምፈልገው ከሜሲ ጋር በድጋሚ መጫወት ነው፤ ከእሱ ጋር በሜዳ ላይ ሆኜ እግር ኳስን ማጣጣም እፈልጋለሁ" ብሎ ነበር።
"ከፈለገ እኔ በምጫወትበት ቦታ ሊጫወት ይችላል፤ ምንም ችግር አይኖረውም። እርግጠኛ ነኝ። እሱ ብቻ ፒኤስጂን ይቀላቀል እንጂ ሌላው አሳሳቢ አይደለም። ከእሱ ጋር በድጋሚ መጫወት ትልቁ ህልሜ ነው። በሚቀጥለው የውድድር ዓመት ይህ እንደሚሆን ደግሞ እርግጠኛ ነኝ" ሲል አስተያቱን ነበር።
ሌሎቹ የፒኤስጂ ተጫዋቾች ዲ ማሪያ እና ቬራቲ እንዲሁም የፒኤስጂ ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ሊአንድሮ ፓሬዴዝ ሊዮኔል ሜሲ ለባርሴሎና መጫወት ካልፈለገ ቡድናቸውን እንዲቀላቀል እንደሚፈልጉ በግልጽ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በባለፈው የውድድር ዓመት ሜሲ ባርሴሎናን እንደሚለቅ ባስታወቀ ጊዜ መዳረሻው በቀድሞው የባርሴሎና አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ሊሆን እንደሚችል በስፋት ሲገለጽ ነበር። እንደውም በሐሳብ ደረጃ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሎም ነበር።
የአሁኑ የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ እአአ ከ2008 ጀምሮ እስከ 2012 ድረስ ለአራት ዓመታት ያህል ሜሲን አሰልጥኖታል። በአራት ዓመት ጊዜውም ሦስት የላሊጋና ሁለት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አንስቷል።
በአንድ ወቅትም "እኔ በጣም እድለኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ቢያንስ የዓለማችን ምርጡን ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲን አሰልጥኜዋለሁ" በማለት ጋርዲዮላ ለሜሲ ያለውን አድናቆት ገልጿል።
ሊዮኔል ሜሲ 644ኛ ጎሉን ለክለቡ ባርሴሎና በማስቆጠር የፔሌን ክብረ ወሰን የሰበረው ታኅሣስ ወር ላይ ነበር።
ሜሲ የከፍተኛውን ግብ ክብረ ወሰን በእጁ ለማስገባት የቻለው ቡድኑ ባርሴሎና ከሪያል ቫላዶሊድ ጋር በነበረው ግጥሚያ ከመረብ ባገናኘው ጎል ነው።
በዚህም ሜሲ ለአንድ ክለብ ብዙ ጎሎች በማስቆጠር የብራዚላዊውን እግር ኳሰኛ ፔሌ ክብረ ወሰን ሰብሯል።
ብራዚላዊው የእግር ኳስ ጥበበኛ ፔሌ ለሳንቶስ ክለብ ከ1956 እስከ 1974 ተጫውቷል። ለ19 የውድድር ዘመኖች ለአገሩ ክለብ የተጫወተው ፔሌ 643 ጎሎች ከመረብ ማገናኘት ችሏል።