የ18 ዓመቷ ወጣት መሰወርን ተከትሎ ቤተሰቧ ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው

ታትሟል

በሰሜን ጣልያን ከሚገኘው የቤተሰብ መኖሪያ ቤት የተሰወረችው የ18 ዓመት ወጣት ዘመዶች በግድያ ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የሳማን አባስ ቤተሰቦች ጋብቻ እንድትፈጽም ወደ ፓኪስታን እንድትሄድ ቢያግባቧትም ሳትፈቅድ ቀርታለች፡፡

አንድ የአጎቷ ልጅም በፈረንሳይ አገር ተይዞ ለጣሊያን ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡

የሳማን አጎት እንደዚሁም አንድ ሌላ የአጎቷ ልጅ መሰወራቸው የተሰማ ሲሆን ወላጆቿ ወደ ፓኪስታን መሸሻቸው ተዘግቧል፡፡

ዓቃቤ ሕግ አምስቱን የቤተሰብ አባላት በግድያ እና አስከሬን በማስወገድ ወንጀል ጠርጥሯቸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ የወጣቷን አስከሬን ማግኘት አልተቻለም፡፡

ወላጅ አባቷ ሳማን ከጠፋች በኋላ ከአንድ ጣሊያናዊ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ልጃቸው ቤልጅየም መሄዷን ተናግረው ነበር፡፡

የጣሊያን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከጥቅምት ወር ጀምሮ በማኅበራዊ አገልግሎቶች ከለላ በሚሰጥ ተቋም ሥር ቆይታ በሚያዚያ ወር መጨረሻ በፓርማ አቅራቢያ ወደሚገኘው የቤተሰቦቿ ቤት ተመልሳለች፡፡

ዓቃቤ ሕግ ኢዛቤላ ቺኤሲ እንደተናገሩት ባለሥልጣናት ወደ ቤቷ እንድትመለስ እንዳታለሏት ያምናሉ፡፡ ሆን ተብሎ የታቀደ ግድያ እንደሆነ እንደሚያምኑ የገለጹት ዓቃቤ ሕጓ ከዚህ በኋላ መልካም ውጤት ይገኛል የሚል ተስፋ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

የወጣቷን አስከሬን ከኖቬላራ አቅራቢያ ባሉ የእርሻ ቦታዎች ላይ ከግንቦት ወር ጀምሮ እያፈላለገ ያለው ፖሊስ አሁን ከአፈሩ ስር ተሸፍና እንደሆነ ለማወቅ የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ዳሳሾችን መጠቀም ጀምሯል፡፡

ባለሥልጣናቱ ተገደለች ብለው ከሚያምኑበት ከሚያዚያ 21 ጀምሮ የደኅንነት ካሜራ ቀረፃ ይፋ አድርገዋል፡፡ በዘህም መሠረት ከተጠርጣሪዎች መካከል ሦስቱ አካፋ፣ ዲጂኖ እና ሰማያዊ ሻንጣ ይዘው ሲሄዱ ያሳያል፡፡

በቀጣዩ ቀንም የጠፋችው ታዳጊ ከወላጆቿ ጋር ከቤት ስትወጣ ያሳያል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት የጣሊያን የእስላማዊ ማኅበረሰቦች ሕብረት የሳማን አባስ መሰወርን ተከትሎ የግዳጅ ጋብቻን ውድቅ በማድረግ ፈትዋ (ሃይማኖታዊ ብይን) ሰጥቷል፡፡