ካናዳ የትራምፕ ደጋፊ ነው የሚባለውን ቡድን አሸባሪ ስትል ፈረጀች

Proud boys

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ካናዳ፤ ፕራውድ ቦይስ የተሰኘውን የአሜሪካ ቀኝ ዘመም አክራሪ ቡድን አሸባሪ ስትል ፈረጀች።

የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትሩ ቢል ብሌይር ካናዳ ውሳኔው ላይ የደረሰችው ቡድኑ ባለፈው ጥር በአሜሪካው ካፒቶል በደረሰው ጥፋት ላይ በመሳተፉ ነው ብለዋል።

ካናዳ ቡድኑ አሸባሪ ነው ብላ በመፈረጇ የቡድኑ ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ ይታገዳል። አልፎም የቡድኑ አባላት ጥፋት አጥፍተው ከተገኙ በሽብር ወንጀል ይከሰሳሉ።

ቡድኑ ወንድ አባላት ብቻ ያሉት ሲሆን በይፋ ፀረ-ስደተኛ እንደሆነ የሚናገርና ብዙ ጊዜ ስሙ ከአመፅ ጋር የሚያያዝ ነው።

በፈረንጆቹ 2016 በካናዳዊው ጋቪን ማክኢንስ ነው ይህ ቡድን የተቋቋመው።

ጋቪን ቫይስ የተሰኘው ሚድያ አጋር መሥራች የነበረ ቢሆንም ቫይረስ ሚድያ ግን ራሱን ከጋቪንም ሆነ ከፕራውድ ቦይስ አግልሏል።

ፕራውድ ቦይስ የተሰኘው ቡድን በቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሚደገፉ ሐሳቦችን ያራምዳል።

በቅርቡ በተደረገው የአሜሪካ ምርጫ ላይ ትራምፕ ለክርክር ከጆ ባይደን ጋር በተሰለፉበት ወቅት የቡድኑን ስም ማንሳታቸው ይታወሳል።

ፕሬዝደንቱ የነጭ የበላይነትን ስለሚያንፀባርቁ ቡድኖች በተጠየቁበት ወቅት ነው 'ለምሳሌ ፕራውድ ቦይስ' ብለው አስተያየት የሰጡት።

በወቅቱ የቡድኑ አባላት ከፕሬዝደንቱ ይሁንታ ተሰጥቶናል በማለት በተጠንቀቅ ቆመው ነበር። ነገር ግን ትራምፕ ወደ ኃላ ራሳቸውን ከቡድኑ ገሸሽ አድርገዋል።

የአሜሪካ ሃገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በአሜሪካ ምርጫ ውጤት ደስተኛ ያልሆኑ ሃገር በቀል አሸባሪዎች አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ ብሎ ማስጠንቀቂያ ካወጣ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው ካናዳ ቡድኑ አሸባሪ ነው ስትል የፈረጀችው።

ካናዳ ይህንን ባወጀች በሰዓታት ውስጥ የአሜሪካ ፍትህ መሥሪያ ቤት የቡድኑ የሲያትል ክንፍ አለቃን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።

የ30 ዓመቱ ኢተን ኖርዲን በአሜሪካ መንግሥት ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት [ካፒቶል] ላይ በደረሰው ግጭት ሳቢያ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ የቡድኑ አባላት ስምንተኛው ነው።

የካናዳው ሚኒስትር በአሁኑ ወቅት ምን ያክል የፕራውድ ቦይስ ክንፍ በሃገራቸው እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ይፋ አላደረጉም።

ነገር ግን 'በርዕዮተ ዓለም የተገፋፉ አክራሪዎች አደጋ ሊሆን ይችላሉ' ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የካናዳው ፕራውድ ቦይስ ከአሜሪካው በተለየ ብዙም የተደራጀ አይደለም ቢባልለትም ካናዳ ቡድኑን በአሸባሪነት መፈረጇ ምናልባትም ቡድኑ የበለጠ የተደራጀ ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥርጣሬን አሳድሯል።

ሚኒስትሩ ካናዳ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው የቡድኑን እንቅስቃሴ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከተከታተለች በኋላ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለው ቡድኑ በካናዳ በተለያዩ ጊዜያት ጥቃቶች ለማድረስ ሞክሯል ብለዋል።

በጣም ሰፊ ድንበር በሚጋሩት ካናዳና አሜሪካ መካከል ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ አለ።

ባለፈው ወር ካፒቶል ላይ በደረሰው ግርግር ላይ ቢያንስ ሁለት ካናዳዊያን ተሳታፊ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ተገምቷል።

የካፒቶሉ ጥቃትን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ ደግሞ አንድ ሰው የካናዳ ባንዲራ ሲያውለበልብ ይታያል።

ካናዳ ፕራውድ ቦይስ የተሰኘውን ተቋም አሸባሪ ስትል የበየነች የመጀመሪያዋ ሃገር ናት። ከዚህ ቡድን ባሻገር ሌሎች ሁለት ቡድኖችም በአሸባሪ ቡድን መዝገብ ላይ ስማቸው ሰፍሯል።

በአጠቃላይ ስድስት የነጭ የበላይነት ሰባኪና የናዚ ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ ቡድኖች አሸባሪ ተብለው ተፈርጀዋል።