1.3 ቢሊየን ጉዞ የተቀነሰበት የቻይናውያን አዲስ ዓመት

ታትሟል

የቻይናውያን አዲስ ዓመት ተቃርቧል። ከኮሮናቫይረስ በፊት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቻይናውያን በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማሳለፍ ከግዛት ግዛት ይጓጓዙ ነበር።

ዘንድሮ በርካታ ቻይናውያን ተጓጉዘው ቫይረሱ እንዳይሰራጭ ለማድረግ መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

ቹንያን በመባል ለሚታወቀው የቻይናውያን አዲስ ዓመት 1.7 ቢሊዮን ሰዎች ይጓጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ስለዚህም ቻይና ለ50 ሚሊዮን ዜጎች (ከአጠቃላይ ሕዝቡ 3.5%) ክትባት ለመስጠት አቅዳለች።

ባለፉት ሳምንታት በተለይም በገጠራማ ቻይና ወረርሽኙ እያገረሸ ነው። ለምሳሌ ቶንጋሁኡን የተባለችው ግዛት የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች።

ይህ ማለት ለበዓል መጓጓዝ ከባድ ነው ማለት ነው። መንግሥት ከኮሮናቫይረስ ነጻ የሆኑ ሰዎች ብቻ እንደሚጓዙ አስታውቋል።

ተጓዦች ለ14 ቀናት ቤት ውስጥ ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩም ይጠበቃል።

ይህ ሕግ ላብ አደሮች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ተብሎ ተተችቷል።

ተማሪው ሆንግ ጂ "በዓል ማሳለፍ ያለብን ከምንወዳቸወ ሰዎች ጋር ነው" ሲል የወጣው ሕግ ጉዞን ፈታኝ እንዳደረገው ይናገራል።

"ሚስቴና ልጆቼን ካገኘሁ ስድስት ወር አለፈኝ"

ሀንግዡ ግዛት ለበዓል አንጓዝም ለሚሉ የቀን ሠራተኞች 113 ዶላር ለመስጠት ውሳኔ አሳልፏል። ሌሎች ግዛቶችም ተመሳሳይ እርምጃ እየወሰዱ ነው።

ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው የገንዘብ ጉርሻና ነጻ ምግብ እንዲሰጡ እንዲሁም ባህላዊ ሥነ ሥርዓት እንዲያዘጋጁላቸውም ተጠይቀዋል።

የቻይና ግዛቶች ሰዎች እንዳይጓጓዙ ለማበረታታት የተለያየ ዘዴ እየተጠቀሙ ነው።

ዩው የተባለ ግዛት ባህላዊ ክንውኖችን ከክፍያ ነጻ እንደሚያቀርብ ይፋ አደርጓል። ለአዲስ ዓመት መደብር ለሚከፍቱ ነጋዴዎች ማበረታቻም ይሰጣል።

በተጨማሪም ነዋሪዎች ህክምና ሲያደርጉ ቅናሽ ይደረግላቸዋል።

"ግዴታ ካልሆነባችሁ በስተቀር አትጓዙ" የሚሉ ፓስተሮች በመዲናዋ ቤጂንግና ሌሎችም ከተሞች ተሰቅሏል።

በአንድ መደብር የሚሠራው ኦፋን ጋዎ እንዳለው፤ አለቃቸው ከቤጂንግ እንዳይወጡ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

"አዲስ ዓመትን ቤጂንግ እንድናሳልፍ ተነግሮናል። ከቤጂንግ የሚወጣ ሰው ማመልከቻ ማስገባት አለበት። ማመልከቻው ተቀባይነት የማግኘት እድሉ 20 በመቶ ነው። ይህ መሆኑ አሳዝኖኛል" ይላል።

እቃ አመላላሹ ሉ፤ ባለቤቱና ልጆቹ ከከተማ ውጪ እንደሚኖሩ ይናገራል። ለበዓል ቤተሰቡን ለማየት እንደጓጓም ያክላል።

"ሚስቴና ልጆቼን ካገኘሁ ስድስት ወር አለፈኝ። ናፍቀውኛል። ትልቅ ከተማ መጥቼ የምሠራው ገንዘብ አግኝቼ ወደእነሱ ለመመስ ነው" ይላል።

ቱሪዝም በአዲስ ዓመት

የቻይና አዲስ ዓመት ለቻይናውያን እንዲሁም ለሌሎች አገራት ቱሪስቶችም ማራኪ ነው።

የቻይናው የጉዞ ወኪል ሲትሪኦእ እንደሚለው ዘንድሮ ሰባት ሚሊዮን ቻይናውያን ቱሪስቶች ለበዓት ይጓዛሉ ተብሎ ተገምቶ ነበር።

የቱሪስቶች ቁጥር የቀነሰው በቻይና ብቻ ሳይሆን በሌሎች የእስያ አገራትም አሽቆልቁሏል።

ታይላንድ፣ ሲንጋፖር፣ ቬትናም፣ ጃፓን እና ማሌዥያ በዚህ የበዓል ወቅት ድንበራቸውን ከዘጉ አገራት መካከል ናቸው።

ቻይና ወደ አገሯ የሚገቡ ሰዎችን ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ ታስገባለች። ከዚያም ለሰባት ቀናት በቤታቸው ሆነው ክትትል ይደረግላቸዋል።

ታይላንድ ውስጥ የሚገኘው ቅንጡ ሆቴል አካርያን መስራችና ኃላፊ አንካሂካ ኪጅኮን "የዘንድሮው አዲስ ዓመት ቀዝቃዛ ነው" ይላል።

በቀደሙት ዓመታት የቻይና አዲስ ዓመት ከቻይና አልፎ ለታይላንድም ቱሪስቶች የሚያስገኝ ነበር።

ዘንድሮ ግን ያለ ቱሪስቶችና ቻይናውያንም እንደ ልባቸው ሳይጓጓዙ በዓሉ ያልፋል።