የቻይና ወንዶችን ያስቆጣችው ኮሜዲያን

የፎቶው ባለመብት, WEIBO
የ 29 ዓመቷ ያንግ ሊ በቻይና ከሚታወቁ ኮሜዲያን አንዷ ናት።
እውቅና ያተረፈችው ባለፉት ጥቂት ወራት ነው። 'ፓንችላየን ክዊን' በሚል ቅጽል ስም ትታወቃለች።
በየሳምንቱ በብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ እየቀረበች አወዛጋቢ የሥነ ጾታ ጉዳዮችን ታነሳለች። ይህ ደግሞ በቻይና የተለመደ አይደለም።
ያንግ ሊ በርካታ ተከታዮች እንዳፈራችው ሁሉ የሚተቿትም አልታጡም።
'ወንዶችን ትጠላለች'፣ 'ወንዶችን ታጣጥላለች' እያሉ የሚከሷት አሉ። ደጋፊዎቿ ደግሞ ወንድ ተመልካቾች 'ስሱ ናቸው'፣ 'ቀልድ አይገባቸውም' ሲሉ ይከላከሏታል።
የምትቀልድባቸው ጉዳዮች ቻይና ውስጥ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ውይይት አጭረዋል።
በቻይና ባህል 'ዢያንግሺንግ' የሚባል ልማድ አለ። ሁለት ኮማኪዎች እርስ በእርስ ሲቀላለዱ የሚታይበት ነው።
በምዕራቡ ዓለም የቀልዱ ታዳሚዎች ላይም ሊቀለድ ይችላል። ይሄ በቻይና እምብዛም አልተለመደም።
በቤጂንግ የቀልድ ክለብ ያለው ቶኒ ቾው እንደሚለው፤ በምዕራቡ ዓለም ቀልድ ሰዎችን ማስቆጣት፣ መፈተን፣ ባለሥልጣኖችና ማኅበራዊ መዋቅር ላይ ጥያቄ ማንሳት ያካትታል።
ቻይና ውስጥ ግን ይህ ክብረ ነክ ተደርጎ ይወሰዳል።
በሱ ክለብ ውስጥ ስለ አንድ የቻይና ማኅበረሰብ የቀለደ ኮማኪ ጥቃት ተሰንዝሮበት እንደነበር ያስታውሳል።
ስለዚህም ብዙ ኮማኪዎች የግል ስሜታቸውን ከታዳሚው መደበቅ ይመርጣሉ።
አስተያየትን በነጻነት መግለጽ ፓለቲካዊ ጫና ሊያሳድር ወይም ከገበያው ሊያስወጣ እንደሚችልም ያምናሉ።
ስለ ኮማኪዋ ያንግ ሊ የተለያየ አስተያየት ይሰነዘራል። አንድ የቻይና ታዋቂ ኮሜድያን ሲያጣጥላት አሜሪካዊ-ቻይናዊ ጆ ዎንግ ግን ችሎታዋን አድንቋል።
ስለ ያንግ የሚሰጠው አስተያየት ቻይና ውስጥ የሥነ ጾታ ጉዳይ ያለውን ቦታም የሚጠቁም ነው።
የጾታ እኩልነት ተሟጋች ነኝ ብላ ባትናገርም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰጣት አስተያየት ከዚህ አቋም ጋር ይገናኛል።
ከተሰጧት የማኅበራዊ ሚዲያ አስተያየቶች አንዱ "የወታደራዊ አቋም ያላቸው የጾታ እኩልነት ተሟጋቾች ምክንያታዊ አይደሉም" ይላል።
ቹ ይን የተባሉ የሕግ መምህር "የምዕራቡ ዓለም የሥነ ጾታ ፓለቲካ የሠራተኛውን ማኅበረሰብ የሚቃረን ነው" ብለዋል።
ከዚህ በተቃራኒው የኮማኪዋ ደጋፊዎች እንደሚሉት፤ ያንድ መተቸቷ የሴቶች እይታ ዋጋ እንደማይሰጠው ማሳያ ነው።
ወንዶች ከሴቶች የተሻሉ ናቸው የሚለው የተዛባ አመለካከት የሴቶችን ሐሳብና አስተያየት ለማጣጣል እንደሚውልም ይናገራሉ።
ቻይና ውስጥ ወንድና ሴት ያላቸው ማኅበረሰባዊ ሚና አሁንም አልተለወጠም።
የሴቶች መብት ተሟጋቿ ዢዎንግ ጂንግ እንደምትለው፤ ወንዶችም ጾታን መሠረት ያደረጉ መድልዎች ይደርሱባቸዋል። እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው፤ ወንዶች ባለ ቤት፣ ባለ መኪና ወዘተ. . . መጠበቁን ነው።
ወንዶች ይህንን የተዛባ አመለካከት መፈተሽ እንዳለባቸውም ታስረዳለች።
ሌላዋ የመብት ተሟጋች ሉ ፒን፤ ቻይና ውስጥ የጾታ እኩልነት ትግል በፓለቲካውና በማኅበራዊ መስተጋብርም ፈታኝ እንደሆነ ትናገራለች።
"በቻይና አባታዊ ሥርዓት ከጾታ እኩልነት ተሟጋቾች ይልቅ ተቺዎች የመንግሥት ድጋፍ አላቸው" ትላለች።
የጾታ እኩልነት ለመፍጠር ሲታገሉ፤ ማኅበራዊ መዋቅርን ሊያፈርሱ ነው ተብለው በቻይና መንግሥት ይተቻሉ።
እአአ በ2015 አምስት የጾታ እኩልነት ተሟጋቾች ለስምንት ሳምንታት ታስረው ነበር። የታሰሩት ወሲባዊ ጥቃትን የሚኮንን ንቅናቄ በማድረጋቸው ነው።
2018 ላይ 'ፌምኒስት ቮይስስ' የተባለው ተቋም ሳንሱር ተደርጓል፤ በተደጋጋሚም ድረ ገጹ ታግዷል።
ሉ እንደምትለው፤ ብዙውን ጊዜ ንቅናቄው 'ከውጪ ኃይሎች' ጋር ይገናኛል ተብሎ ይኮነናል።
ኮማኪዋ ያንግ ሊ የገጠማትም ይህንኑ አይነት ውዝግብ ነው።
በቻይናው ማኅበራዊ ሚዲያ ዊቡ ላይ የተጻፈ መልዕክት ያንግ ምርመራ እንዲደረግባት ይጠይቃል። ይህ መልዕክት የኋላ ኋላ ጠፍቷል።
መንግሥት ኮማኪዋ ላይ ምርመራ ስለመክፈቱ ምንም መረጃ የለም።
ኮማኪዋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ ላይ "ማብቂያ የለውም. . . እዚህ ዘርፍ ውስጥ መቆየት ከባድ ሆኗል" ከማለት ውጪ ከቢቢሲ ለቀረበላት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠችም።












