ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ፡ ፈረንሳይ የኮቪድ-19 ክትባት የመስጠት ሂደትን ልታፋጥን ነው
በመጀመሪያው ሳምንት ውስጥ 516 ክትባቶች ብቻ የሰጠው የፈረንሣይ መንግሥት የኮሮናቫይረስ የክትባት በዝግታ እየሄደ ነው በሚለው የሚቀርብበተን ትችት ተከላክሏል።
መዘግየቱ በአቅርቦት ምከንያት ነው ያሉት የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ገብርኤል አታል ለዚህም በእንክብካቤ መስጫዎች ውስጥ አዛውንቶችን መጎብኘትና የእያንዳንዱን ሰው ፈቃድ ማግኘት አስፈላጊ ነበር ብለዋል።
የአውሮፓ ሕብረት አገራት ከሳምንት በፊት ጀምሮ የፋይዘር/ባዮኤንቴክ ክትባቶች መስጠት መጀመራቸው ይታወሳል።
እስከ እሁድ ጠዋት ድረስ በጀርመን 240 ሺህ ያህል ክትባቶች ተሰጥተዋል።
እንግሊዝ የኦክስፎርድ አስትራዜኔካ የኮሮናቫይረስ ክትባትን በመስጠት የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች። ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ፋይዘር/ባዮኤንቴክን ክትባት አግኝተዋል።
ጋብሪል አታል እንደተናገሩት መንግሥት ሳይንሳዊ ምክሮችን እየተከተለ በእንክብካቤ መስጫ ላሉ አረጋውያን ቅድሚያ ይሰጣል።
"በሎጂስቲክ ምክንያቶች የበለጠ ቀስ በቀስ ማስጀመር አስፈላጊ ነው። እነዚህ ሰዎች በአገሪቱ ውስጥ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ መጠየቅ አይቻልም። መዘግየቱ ከቅድመ ክትባት ምክክር እና ፈቃድ ከማግኘት ጋርም የተቆራኘ ነው። ይህ ትንሽ ጊዜ ይወስዳል" ብለዋል።
በአውሮፓ በወረርሽኙ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አገራት መካከል ፈረንሳይ አንዷ ናት።
ወደ ኋላ የቀረችው ኔዘርላንድስ
በአውሮፓ ሕብረት ሁሉን አቀፍ ፈቃድ መሠረት ፈረንሳይ ክትባቶችን ባለፈው ሰኞ መስጠት ጀምራለች። ከሕብረቱ አባል አገራት መካከል ኔዘርላንድስ የክትባት ዘመቻዋን አስካሁን ያልጀመረች ሲሆን ከአራት ቀናት በኋላ መክተብ ትጀምራለች ተብሏል።
አታል "ከሁለት ሚሊዮን በላይ ክትባቶች አዘጋጅተናል" ያሉ ሲሆን በጥር ወር መጨረሻ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ለመከተብ የተያዘውን ዕቅድ እንደሚያሳኩ አጥብቀው ተናግረዋል።
ከፈረንሣይ የጤና ባለሥልጣናት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው እስከ ጥር አርብ ዕለት 516 ሰዎች ክትባቱን አግኝተዋል።
አንድ ሚሊዮን ሰዎችን የመድረስ ዒላማውን ለመምታት ወደ 35 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በየቀኑ መከተብ ይኖርባቸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት እስካሁን የፈቀደው የፋይዘር/ባዮኤንቴክ ክትባትን ብቻ ነው። ክትባቱ ቤልጂየም ውስጥ ፑርስ በሚባል ፋብሪካ ውስጥ ነው የሚመረተው።
የጀርመን መንግሥት የሞዴሬና ክትባት ረቡዕ ዕለት የአውሮፓ ሕብረትን ፈቃድ ያገኛል ብሎ ይጠብቃል።
እንደአታል ከሆነ የፈረንሣይ የክትባት ዘመቻ በዚህ ሳምንት "መንገዱን በመያዝ ይጠናከራል" ብለዋል። ከረቡዕ ጀምሮ "በፈረንሣይ የሚገኙ 94 የህክምና ማዕከላት ለጤና ባለሙያዎች የሚሰጡት ከ500 ሺህ በላይ የክትባቱ ብልቃጦች ይኖራቸዋል" ብለዋል።