ኮሮናቫይረስ ፡ ሕንድ ለሁለት አምራቾች የኮቪድ-19 ክትባት ማረጋገጫ ሰጠች

ታትሟል

አንድ ዓመት ያስቆጠረውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የተለያዩ አገራት ክትባት መስጠት ከጀመሩ ጥቂት ሳምንታት ሆኗል። ይህንን ዘመቻ የተቀላቀለችው ሕንድም ሁለት የኮሮናቫይረስ ክትባቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይፋዊ ማረጋገጫ ሰጥታለች።

አስትራዜኔካ ከኦክስፎርድ ጋር በመተባበር እና ባራት ባዮቴክ ያዘጋጇቸውን ሁለት ክትባቶች ሕንድ ጥቅም ላይ እንድታውል የአገሪቱ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ማረጋገጫ ሰጥቷል።

ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ ውሳኔውን "ወሳኝ ምዕራፍ" ብለውታል። ሕንድ በዚህ ዓመት እስከ 300 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ እቅድ ይዛለች።

በዓለም ላይ በኮሮናቫይረስ በመጠቃት ሁለተኛዋ አገር የሆነችው ሕንድ፣ እስካሁን 10.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎቿ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል። 150 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ በዚሁ የኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።

1.3 ቢሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ሕንድ፣ ትናንት [ቅዳሜ] ክትባቱን ለማሳለጥ በመላ አገሪቱ 90 ሺህ የሚሆኑ የጤና ሞያተኞችን አሰማርታለች።

የኦክስፎርድ/አስትራዜኒካ ክትባት ሴረም በተባለ የሕንድ ተቋም የተመረተ ክትባት ነው። ይሄው ፋብሪካ በወር 50 ሺህ የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን እያመረትኩ ነው ብሏል።

የሕንድ የመድኃኒት ቁጥጥር ዋና ባለስልጣን እንዳሉት ሁለቱም አምራቾች ክትባቶቻቸው ደኅንነታቸው በተረጋገጠ ሁኔታ ማምረት እንደሚችሉና ለጥቅም ዝግጁ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ባለፈው ኅዳር ወር ላይ ማረጋገጫ ካገኙ በኋላ ቢያንስ በወር 100 ሚሊዮን ክትባት ለማምረት ማቀዳቸውን ገልጸው ነበር።

በሕንድ ኮቪሼልድ የሚል ስያሜ የተሰጠው ክትባቱ ሁለት ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን ከ4 እስከ 12 ሳምንታት ባለው ልዩነት ውስጥ የሚሰጥ ይሆናል።

ክትባቱ የሚቀመጥበት ቦታም ከ2 እስከ 8 ሴልሽየስ በሆነ የቅዝቃዜ መጠን ሊሆን እንደሚገባ ተነግሯል። ይህም ክትባቱን ለማሰራጨት ቀላል ያደርገዋል ተብሏል።

በሌላ በኩል በፋይዘር/ባዮንቴክ የሚመረተው ክትባት በ70 ሴልሽየስ የቅዝቃዜ መጠን መቀመጥ እንዳለበት ይመከራል። መንቀሳቀስ የሚችለውም ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ነው ተብሏል። ይህ ደግሞ በሕንድ የሙቀት መጠኑ 50 ሴልሽየስ በሚደርስበት ጊዜ የክትባት አቀማመጥና አሰጣጡን ፈታኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የዓለምን 60 በመቶ ክትባት የምታመርተው ሕንድ እስከሚቀጥለው ሐምሌ ድረስ 300 ሚሊዮን ዜጎቿን ለመከተብ አቅዳለች። የጤና ሙያተኞችን፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞችንና በእድሜ የገፉ ሰዎችን ቅድሚያ ለመስጠትም ሕንድ ግብ አስቀምጣለች።

በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአውሮፓ ሕብረት ትግበራ ላይ የሚገኘው ፋይዘርም በሕንድ ፈቃድ ይሰጠኛል ብሎ በመጠባበቅ ላይ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ 30 የሚደርሱ የኮሮናቫይረስ ክትባቶች በሕንድ እየበለጸጉ ነው።