ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እርግብ ፡ አንድ እርግብ በ2 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠች
አንድ የቤልጂየም እርግብ በጨረታ ታሪክ በከፍተኛ ዋጋ ተሽጣለች። ይህም ሁለት ሚሊዮን ዶላር ወይም 70 ሚሊዮን ብር አካባቢ ነው።
እንዴት አንድ እርግብ በዚህን ያህል ዋጋ ይሸጣል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።
እርግቧ በዚህ ዋጋ ሊሸጥ የቻለው እጅግ ፈጣን በራሪ እርግብ በመሆኗ ነው። በዓለም ላይ ተወዳጅ እየሆነ የመጣው "የእርግቦች ማራቶን" ፈጣን እርግቦች በውድ ዋጋ በጨረታ እንዲሸጡ ምክንያት እየሆነ ነው።
የዚች እርግብ ስም 'ኒው ኪም' ይባላል። የጨረታዋ መነሻ ዋጋዋ 200 ዩሮ ነበር። አንድ ቻይናዊ የእርግብ ማራቶን አፍቃሪ ግን በታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ ዋጋ አቅርቦ ወስዷታል።
የእርግቧ ቀዳሚው ባለቤት ኩርት ቫን ዲ ዉመር የዚች እርግብ አሳዳጊ ሲሆን በቀረበው የገንዘብ መጠን እሱም ቤተሰቡም መደንገጣቸውን አምኗል።
ከዚህ እርግብ በፊት ውድ ሽያጭ የተመዘገበው ለ4 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ እርግብ ሲሆን አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ነበር የተሸጠው፤ የዛሬ ዓመት።
'አርማዶ' የተባለው ይህ እርግብ ቅጽል ስሙ 'ልዊስ ሐሚልተን' ሆኖም ነበር። ልዊስ ሐሚልተን የፎርሙላ ዋን የመኪና ውድድር የዓለም ሻምፒዮን እንደሆነ ይታወቃል። አሁን አርማዶ እርግብ ጡረታ የወጣ ሲሆን ዝርያው በጣም ተፈላጊ ሆኗል።
አሁን በውድ ዋጋ ክብረ ወሰን የሰበረችው ኒው ኪም የተሰኘችው እርግብ በ2018 የእርግቦች ማራቶን አሸናፊ ነበረች።
ኒው ኪም እንደ አርማንዶ ሁሉ በጨረታ የተገዛችው በቻይና ባለሀብት ነው። እንደእሷ ያሉ ፈጣን በራሪ እርግቦችን መንታ መንታ ትወልዳለች ተብሎ ተጠብቋል።
በቻይና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእርግብ ማራቶን ተወዳጅ እየሆነ መጥቷል። የእርግብ ማራቶን የቢሊዮን ዶላር ኢንዱስትሪ ሲሆን በርካታ ደጋፊዎችና አፍቃሪዎችም አሉት።
እርግቦች ከሚኖሩበት ቦታ በሺህ ኪሎ ሜትር ርቀው በእኩል ሰዓት ይለቀቃሉ። ጂፒኤስ እግራቸው ላይ ተገጥሞላቸው ስለሚለቀቁ ጉዟቸውን ለመከታተል ቀላል ነው።
ፈጣኑ በራሪ እርግብ ታዲያ ከፍተኛው ተሸላሚ ይሆናል። የእርግቦች ማራቶን ውድድር በርካታ ርቀትን የሚሸፍን ሲሆን እርግቦች ወደ መነሻቸው የሚመለሱት በሺህ ኪሎ ሜትር አቋርጠው ከ10 ሰዓታት በላይ ተጉዞው ሊሆን ይችላል። እርግቦቹ በረዥም ርቀት በረራቸው መሀል አረፍ እያሉ ውሀ ሊጠጡ ምግብ ሊቀማምሱ ይችላሉ።
ሺህ ኪሎ ሜትር በሚሸፍን በአንድ የእርግብ ማራቶን ብቻ ከ20 ሺህ በላይ ተወዳዳሪ እርግቦች ሊሳተፉ ይችላሉ።
ብዙውን ጊዜ ወንድ እርግቦች ከፍተኛ የጨረታ ዋጋ ይስባሉ። ይህም ብዙ እርግብ ሲያስወልዱ ዝርያቸውና የበረራ ፍጥነታቸው ወደ ጫጩት እርግቦች ስለሚተላለፍ ነው። አሁን በክብረ ወሰን የተሸጠችው እርግብ ግን ሴት መሆኗ አነጋጋሪ ሆኗል።
ቤልጂየም ፈጣን በራሪ ተወዳዳሪ እርግቦችን በማራባት ትታወቃለች። በአገሪቱ ከ20 ሺህ በላይ የማራቶን ተወዳዳሪ እርግቦች እንዳሉ ይገመታል። ይህም ለአገሪቱ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሆኗል።
እርግቦች በዓለም ዋና ዋና የጦርነቶች ታሪክ ውስጥ ወሳኝ መልዕክት ወደ ዋና ዕዝ በማድረስ ሰፊ አገልግሎት መስጠታቸው በታሪክ የተሰነደ ሐቅ ነው።