ኒው ዚላንድ፡ ጀሲንዳ አርደን በድጋሚ ይመረጣሉ?

ታትሟል

በኒው ዚላንድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ድምጽ ሰጥተዋል። እስካሁን ባለው ቆጠራ ጠቅላይ ሚንስትር ጃሲንዳ አርደን በድጋሚ የማሸነፍ እድላቸው ሰፊ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሯ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ያደረጉት ጥረት የብዙዎችን ድምጽ እንዲያገኙ ሳይረዳቸው አልቀረም።ዋናው ጥያቄ ግን በፓርላማ አብላጫ ድምጽ ያገኛሉ? የሚለው ነው።

አብላጫ ድምጽ ያገኛሉ?

የምርጫ ኮሚሽን እንደሚለው፤ የጃሲንዳ አርደን ሌበር ፓርቲ 50 በመቶ ያህል ድምጽ አግኝቷል። ቀኝ ዘመሙ ናሽናል ፓርቲ 26%፣ ግሪን ፓርቲ ደግሞ 9% አግኝተዋል።

ዋናው ጥያቄ የጃሲንዳ ፓርቲ በፓርላማ አብላጫ ድምጽ ያገኛል? የሚለው ነው። ኒው ዚላንድ ፓርላማ ውስጥ ቅይጥ የአባላት ውክልና ከተጀመረ ወዲህ የትኛውም ፓርቲ አብላጫ ድምጽ አላገኘም።

ኦክላንድ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ፕ/ር ጄነፈር ከንተን እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም አብላጫ ድምጽ ያገኛሉ ተብለው የተጠበቁ ተወዳዳሪዎች ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

"መራጮች ዘደኛ ናቸው። ድምጻቸውን ከፋፍለው ይሰጣሉ። ወደ 30 በመቶ መራጮች ድምጻቸውን ለአነስተኛ ፓርቲ ይሰጣሉ። ስለዚህ ሌበር ከ50 በመቶ በላይ ላያሸንፍ ይችላል።"

ጆን ጃን ቬን የተባሉ ተንታኝ ሌበር ከግሪን ጋር ጣምራ ፓርቲ የሚመሠርትበት እድል ሰፊ ነው ይላሉ።

ጃሲንዳ አርደን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የወሰዱት እርምጃ በርካታ ድምጽ እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ይስማማል።

"ዓመቱ መባቻ ላይ ቃል የገቡትን አላደረጉም የሚል ቅሬታ ነበር። ሲመረጡ የልጆች ድህነትና ቤት ማጣትን ለመቅረፍ ቃል ገብተው ነበር። ከምርጫ በኋላ ዝናቸው ይከስማል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

የመራጮች ጥያቄ ምንድን ነው?

ጃሲንዳ የአየር ንብረት ለውጥን ከግምት ያስገቡ ፖሊሲዎች ለማርቀቅ ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም የአቅመ ደካማ ትምህርት ቤቶችን ድጋፍ ለማጠናከር እና የከፍተኛ ተከፋዮችን ገቢ ግብር በሁለት በመቶ ለመጨመር ተስማምተዋል።

ተቀናቃኛቸው ጁዲት ኮሊንስ ናቸው። 'ክራሸር' ወይም 'ደምሳሿ' በሚል ቅጽል ስም ይታወቃሉ።

የ61 ዓመቷ የቀድሞ ጠበቃ የናሽናል ፓርቲ አባል ናቸው። ፓርቲው መሠረተ ልማት ላይ የገንዘብ ፈሰስ ለመጨመር፣ እዳ ለመክፈል፣ በጊዜያዊነት ግብር ለመቀነስ ሐሳብ አለው።

ተንታኙ እንደሚሉት፤ ሁለቱ ፓርቲዎች በአመራር ረገድ ልዩነት አላቸው።

"ጃሲንዳ አርደን ደግ እና አዛኝ አመራር ይከተላሉ። ጁዲት ኮሊንስ ደግሞ ነገሮች በቁጥጥራቸው ስር እንደሆነ እንዲሰማቸው የሚፈልጉ ሰዎች ድጋፍ አላቸው።"

ሁለቱ ሕዝበ ውሳኔዎች

ኒው ዚላንዳውያን ከምርጫው ጎን ለጎን ሁለት ጉዳዮች ላይ ሕዝበ ውሳኔ ያሳልፋሉ። አንደኛው በፍቃድ ሕይወትን ማሳለፍ ሲሆን ሌላኛው እጸ ፋርስን ሕጋዊ ማድረግ ነው።

በተለይም በጠና የታመሙ ሰዎች በሕክምና እርዳታ ሕይወታቸውን እንዲያሳልፉ ይፈቀድ? የሚለው ድንጋጌ፤ ከ50% በላይ አወንታዊ ምላሽ ካገኘ ይተገበራል።

ሌላው ጉዳይ ደግሞ እጸ ፋርስ በሕክምና የታዘዘላቸው ሰዎች እንዲጠቀሙ የረቀቀው ደንብ ነው።

አብዛኛው ሰው ቢስማማም እጸ ፋርስ መጠቀም በአንድ ጊዜ ሕጋዊ አይሆንም። አዲስ የሚመረጠው አስተዳደር ሕጋዊ የሚሆንበትን አሠራር ማርቀቅ ይጠበቅበታል።