ኒው ዚላንድ፡ መስጅዶችን ያሸበረው ግለሰብ ምን ፍርድ ይጠብቀዋል?

ታትሟል

ከወራት በፊት ኒው ዚላንድ ውስጥ ሁለት መስጅዶችን አሸብሮ 51 ሰዎችን የገደለው ግለሰብ ጉዳይ ችሎት ቀርቧል።

ሰውዬው ከሁለቱ መስጅዶች አልፎ ሶስተኛ መስጅድ ሄዶ ጥፋት ሊፈፅሞ አስቦ እንደነበርም ተገልጿል።

ብሬንቶን ታራንት የተባለው ግለሰብ መስጅዶችን በእሳት ዶጋ አመድ ሊያደርግ አቅዶ እንደነበር አቃቤ ሕግ አስታውቋል።

የ29 ዓመቱ ታራንት አመክሮ አልባ የዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ሊፈረድበት ይችላል ተብሏል። ይህ እውን ከሆነ በኒው ዚላንድ ታሪክ የመጀመሪያው ይሆናል ማለት ነው።

ተጠርጣሪው ጥቃቱን እየፈፀመ በፌስቡክ ቀጥታ ሲያስተስላለፍ ነበር።

51 ሰዎችን የተገደሉበት ይህ ጥቃት ኒው ዚላንድ ብቻ ሳይሆን መላው ዓለምን አሸብሮ ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደን መንግሥት በጦር መሣሪያ ዙሪያ ጠበቅ ያለ ሕግ ያወጣውም ከዚህ በኋላ ነው።

በነጭ የበላይነት የሚያምነው ግለሰብ ፍርድ ጥፋቱን በፈፀመባት የክራይስትቸርች ከተማ መታየት የተጀመረው ሰኞ ማለዳ ነው።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ችሎት ኦና ሆኖ ታይቷል። ነገር ግን በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ግለሰቦች በሰባት የተለያዩ ፍርድ ቤቶች ተገኝተው ችሎቱን በቴክኖሎጂ እገዛ ታድመዋል።

ዋና አቃቤ ሕግ ባርናቢ ሃውስ፤ ሰውዬው ጥቃቱን ለመፈፀም ለዓመታት ሲያቅድ እንደነበርና በተቻለው መጠን ጉዳት ለማድረስ ሃሳብ እንደነበረው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ኒው ዚላንድ ውስጥ ስለሚገኙ መስጂዶች አድራሻ፣ ግንባታ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች ሲያሰባስብ ነበር የከረው ተብሏል።

ጥቃቱን ከመፈፀሙ ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ክራይስት ቸርች ከተማ አምርቶ ዋነኛ ዒላማው ከነበረው አል ኑር መስጅድ አናት ሰው አልባ በራሪ [ድሮን] ተጠቅሞ እንደሰለለ ችሎቱ ተመልክቷል።

ከአል ኑር መስጅድ በተጨማሪ አሽበርተን መስጅድና ሊንውድ ኢስላሚክ ሴንትረ የተባለ ተቋም ዒላማው ነበሩ።

ተጠርጣሪው አል ኑር መስጅድ ላይ ጥፋት ፈፅሞ ሲመለስ ሌሎች ሰው ላይ ጥቃቱን አድርሷል። ከእነዚህም መካከል አንሲ አሊባቫ የተሰኘች ሴት አንዷ ስትሆን በመኪና ረግቷት አልፏል ተብሏል።

በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ቃሉን ለፖሊስ የሰጠው ታራንት እቅዱ የተቻለውን ያክል መስጅዶችን ማውደም እንደነበረና ባለማድረጉም እንደተቆጨ ተናግሯል።

ተጠርጣሪው ቢያንስ የ17 ዓመት እሥር ይጠብቀዋል ቢባልም በኒው ዚላንድ ታሪክ ታውቆ በማያውቅ ሁኔታ የዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ሊፈረድበት ይችላል።