ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ፡ አረጋዊያንን በመጦሪያና ማገገሚያ ማዕከላት ውስጥ በአካል ሄዶ መጠየቅ ተከለከለ
የኢትዮጰያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሳቢውን የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመግታትና ዋንኛ ተጠቂ የሆኑ ዜጎችን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲባል፤ ዜጎች በመጦርያና ማገገምያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ አረጋዊያንን በአካል ሄደው ከመጠየቅ እንዲቆጠቡ አሳሰበ፡፡
ተቋሙ መስከረም 30/2013 ዓ. ም. ባወጣው ዘለግ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ከዚህ ዕለት በኋላ ተግባራዊ የሚደረጉ ልዩ ልዩ መመርያዎችን በዝርዝር አስተላልፏል፡፡
ኮቪድ-19 ከተከሰተ ወዲህ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል አቋቁሞ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኘው ተቋሙ፤ ወረርሽኙን ለመከላከልና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ስለሚወሰዱ ክልከላዎች እና ግዴታዎች በሕግ መወሰን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው መመሪያዎቹን ያወጣሁት ብሏል።
በመመርያው መሠረት፤ ማንኛውም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርግ መንቀሳቀስ የከለከለ ሲሆን፤ ከዚህ ክልከላ ነጻ የሆኑት ዕድሜያቸው ከስድስት ዓመት በታች ያሉ ህጻናት እና በማስረጃ የተረጋገጠ የመተንፈሻ አካላት ችግር ያለባቸው ዜጎች ብቻ ናቸው፡፡
አገልግሎት ሰጪዎችን በተመለከተ፤ ማንኛውም መንግሥታዊ የሆነና መንግሥታዊ ያልሆነ የግል ተቋም ሠራተኞች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ተጠጋግተው እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ በጥብቅ ደንግጓል፡፡
ይህም ብቻም ሳይሆን የንግድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ላላደረገ ሰው አገልግሎት መስጠትን ክልክል አድርጓል፡፡
የግልና የመንግሥት የትምህርት ተቋማትም በአካል ተቀራርቦ ትምህርት መስጠት መጀመር እንዳለበት ይፋ ሳይደረግ ማንኛውንም ተማሪ ማስተናገድ እንደሌለባቸው ተወስቷል፡፡
በተለይም የህጻናት ማቆያ ማዕከሎች አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ሳይወሰንና አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ በተመለከተ በመመሪያ ሳይወጣ አገልግሎት መስጠት አይችሉም።
የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በሕግ ከተወሰነው የመጫን አቅም በላይ ሰዎችን መጫን አይችሉም ይላል መመርያው፡፡
በተለይ ደግሞ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረጉ ሰዎችን አገልግሎት መስጠት የለባቸውም ብሏል፡፡
የግንባታ ፕሮጀክት አሠሪዎች በተመለከተ፤ በግንባታ ቦታዎች ላይ አስፈላጊውን ንጽህና ለመጠበቅ የሚረዱ ግብአቶች ሳይሟሉ ሠራተኞችን ማሠራት ክልክል እንደሆነ በመግለጫው አሳስቧል፡፡
መመርያው ሃይማኖታዊ እና የአደባባይ በዓላት አከባበርን በተመለከተ እንዲሁም የጭፈራ፣ ሲኒማ፣ ቴአትር እና የሥዕል ጋላሪ ቤቶች በምን መንገድ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው እንዲሁም ተግባራዊ ማድረግ ስለሚገባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
የወረርሽኙ ስርጭት ያለበት ሁኔታ በየጊዜው እየታየ ሌላ መመሪያ እስኪወጣ ድረስ የአረጋዊያን የመጦሪያ ስፍራዎች እና የማገገሚያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በአካል መጠየቅ በጥብቅ የከለከለ ሲሆን፤ በመመሪያ የተደነገጉ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን የተላለፈ ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው የወንጀል ሕግ መሰረት ተጠያቂ ይሆናል ተብሏል።
ይህ መመርያው ተግባራዊ የሆነው ከመስከረም 25/2013 ዓ. ም. ጀምሮ ነው፡፡