የዓለም ጤና ድርጅት ተፈጸመ የተባለውን ወሲባዊ ጥቃት እመረምራለሁ አለ

ጥቃት የደረሰባት ሴት

የፎቶው ባለመብት, THOMSON REUTERS FOUNDATION

ታትሟል

የዓለም ጤና ድርጅት በዲሞክራቲክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝነን ለመቆጣጠር የተሰማሩ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሰዋል መባሉን እንደሚያጣራ አስታወቀ።

የዓለም ጤና ድርጅት እና የሌላ የተራድኦ ድርጅት ሠራተኞች በዲሞክራቲክ ኮንጎ ወሲባዊ ጥቃት አድርሰዋል የሚል ክስ ቀርቧል። ክሱን ያቀረቡት 50 የሚሆኑ ሴቶች ናቸው።

ጥቃት ደረሰብን የሚሉት ሴቶች በመጠጥ ተታለው፣ በሆስፒታል ውስጥ ተገደው ወሲብ እንዲፈጽሙ መገደዳቸውን እና ከነሱም መሀል ሁለቱ ማርገዛቸውን ይናገራሉ።

ተፈጸሟል የተባለው ወሲባዊ ትንኮስ እአአ ከ 2018 እስከ 2020 የዘለቀ ሲሆን 'ዘ ኒው ሂዩማኒቴሪያን' የተባለ የዜና ወኪል እና ሬውተርስ ፋውንዴሽን በጉዳዩ ላይ ለአንድ ዓመት የዘለቀ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራቸውን ይፋ አድርገዋል።

ሁለቱ ድርጅቶች ይፋ ባደረጉት ዘገባ መሠረት አብዛኛው ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽመዋል የተባሉት የዓለም ጤና ድርጅት ተቀጣሪ የሆኑ ወንዶች ናቸው።

ቢያንስ 30 ሴቶች ወንዶቹ ወሲባዊ ጥቃት እንደፈጸሙባቸው በዜና ወኪሎች ምርመራ ላይ ተመልክቷል።

8 ሴቶች ደግሞ የዲሞክራቲክ ኮንጎ ጤና ሚንስቴር ባልደረባ በሆኑ ወንዶች ጥቃት ተፈጽሞብናል ብለዋል።

በዜና ወኪሎቹ ሪፖርት ላይ ሁለት ሌላ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ስም ተጠቅሷል። ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽመዋል የባሉት ግለሰቦች ደግሞ ከቤልጂየም፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጊኒ ኮናክሪ እና አይቮሪኮስት የመጡ ናቸው ተብሏል።

ይህ ሪፖርት የዓለም ጤና ድርጅት መልካም ስምና ዝና ላይ ጥላሸት ይቀባል የተባለ ሲሆን፤ ድርጅቱም ጉዳዩን ከሥር መሠረቱ እንደሚያጣራ ቃል ገብቷል።

"በዚህ ጥቃት የተሳተፉ ተጠያቂ ይሆናል። እስከ መባረር የሚደርስ ውሳኔም ይተላለፋል" ብሏል ድርጅቱ ባወጣው የጽሑፍ መግለጫ።

በሪፖርቱ ቃላቸው ከሰጡ ሴቶች መካከል የ25 ዓመቷ የጽዳት ሠራተኛ የሥራ ዕድገት ልታገኝ ስለምትችልበት ሁኔታ ለመነጋገር የዓለም ጤና ድርጅት የጤና ባለሙያ ወደሆነ ሰው ቤት ተጋብዛ እንደሄደች ትናገራለች።

"በሩን ዘጋው እና 'ቅድመ ሁኔታ አለው። አሁኑኑ ወሲብ መፈጸም አለብን' አለኝ" በማለት ትናገራለች።

"ልብሴን ማውለቅ ጀምረ። ወደ ኋላ እየሸሸው ልብሴ እንዳያወልቅ ስነግረው በኃይል ልብሴን ማውለቅ ጀመረ። እያለቀስኩ በሩን ከፍቼ በእሩጫ ወጣሁ" ብላለች።

ከኢቦላ በሽታ ያገገመች ሌላ የ32 ዓመት ሴት እንደተናገረችው ከሆነ ደግሞ ለምክር አገልግሎት ወደ አንድ ሆቴል ተቀጥራ ትሄዳለች።

የለስላሳ መጠት ከቀረበላት በኋላ "እራሴን ያገኘሁት ብቻዬን በሆቴል ክፍል ውስጥ እርቃኔን ሆኜ ነው ትላለች" ተገዳ መደፈሯንም ታምናለች።

በዜና ወኪሎቹ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው በሴቶች ላይ የወሲብ ጥቃቱ የተፈጸመው ሥራ ታገኛለችሁ በሚል ምክንያት ነው።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ተከስቶ በነበረው የኢቦላ በሽታ ከ2ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል።