የሴቶች ጥቃት፡ በሕንድ በቡድን የተደፈረች ወጣት መሞትን ተከትሎ ቁጣ ተቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሕንድ የ19 ዓመት ወጣት በአራት ወንዶች ከተደፈረች በኋላ ለሕልፈት መዳረጓን ተከትሎ ቁጣ ተቀሰቀሰ።
ወጣቷ በተፈፀመባት ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ካጋጠማት በኋላ ደልሂ በሚገኝ ሆስፒታል የገባችው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር።
ጥቃቱ የተፈፀመባት በሕንድ ሰሜናዊ ግዛት ኡታራ ፕራደሽ ሲሆን ጥቃት አድራሾቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል።
ፖሊስ አራቱ ወንዶች ወጣቷን በመጎተት ሃትራስ አካባቢ ወደሚገኝ ሜዳ በመውሰድ እንደደፈሯትና ወጣቷ በሚያሳዝን ሁኔታ ለጉዳት መዳረጓን ለአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።
የሟች ወንድምም የእህቱ ሕይወት ማለፉን አረጋግጦ፤ ጥቃቱ በተፈፀመባት የመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት በፖሊስ የታሰረ ሰው አለመኖሩን ተናግሯል።
"ለሞት ተዳርጋለች፤ ለ14 ቀናት ያህል ሕይወቷን ለማሰንበት ታግላለች" ብሏል እህቱ ስለነበረችበት ሁኔታ ሲያስረዳ።
ቤተሰቦቿ በበኩላቸው ወንጀሉን ፈፅመዋል የተባሉት ግለሰቦች በአካባቢው ልጃቸውን ይተነኩሷት እንደነበር ለኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣ ተናግረዋል።
የወጣቷ ሕልፈት ከተሰማ በኋላም በመላው ሕንድ ቁጣ ተቀስቅሷል። በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በመውጣትም ፍትህ እየጠየቁ ነው። በግዛቷ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ድርጊቱን አውግዘዋል።
የቀድሞ የግዛቷ ሚኒስተርና ፖለቲከኛው ማያዋቲ "መንግሥት ለተጎጂዋ ቤተሰቦች አስፈላጊውን እርዳታ ማድረግ አለበት፤ ድርጊቱን የፈፀሙትም በአፋጣኝ ፍርድ ቤት ቀርበው መቀጣት አለባቸው" ብለዋል በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ።
ሌላኛው የቀድሞ ሚኒስትር አኪሂሌሽ ያዳቭ በበኩላቸው መንግሥት በሴቶች ላይ ለሚፈፀሙ ጥቃቶች ግድ የለሽ ነው ሲሉ ተችተዋል።
የሕንድ ሕግ የተደፈረችን ሴት ስም በጋዜጣም ሆነ በሌላ ሚዲያ እንዲጠቀስ አይፈቅድም። በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ኒርብያህ [ፍርሃት የለሽ] በመባል ይጠሯቸዋል።
ስያሜው የመጣው ከስምንት ዓመታት በፊት ዓለምን ባነጋገረውና በደልሂ በአውቶብስ ውስጥ በተፈፀመባት በቡድን የመደፈር ጥቃት ለሞተችው ተማሪ መጠሪያ ሲጠቀሙበት የነበረውን ስም በማስታወስ ነው።
የ23 ዓመቷ የፊዚዮቴራፒ ተማሪ ስሟን መጥቀስ ስለማይፈቀድ በሚዲያ ዘንድ 'ኒርብሃያ' የሚል መጠሪያ ተሰጥቷት ነበር።
በሕንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ካስከተለውና አገሪቷ ያላትን የአስገድዶ መድፈር ሕግ እስከ መለወጥ ካደረሳት በጎርጎሮሳዊያኑ 2012 ተማሪዋ ላይ ከተፈፀመው ጥቃት ወዲህ፤ የመድፈር ወንጀልና ወሲባዊ ጥቃት በህንድ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ይሁን እንጂ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች አሁንም አልቀነሰም።












