በእንግሊዝ ራሳቸውን ለይተው የማያቆዩ እስከ 10ሺህ ፓውንድ ይቀጣሉ ተባለ

ታትሟል

በእንግሊዝ የኮሮናቫይረስ ሥርጭት መጨመሩን ተከትሎ መንግሥት ጥብቅ ክልከላቸዎችን እየጣለ ይገኛል።

ሰዎች እራሳቸውን ለይተው እንዲያቆዩ ተነግሯቸው ሳይፈጽሙ የሚቀሩ ከሆነ እስከ 10ሺህ ፓውንድ ወይም 474ሺህ ብር ገደማ ድረስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

ከዛሬ ጀምሮ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ወይም በኮሮናቫይረስ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳለቸው የተነገራቸው ሰዎች እራሳቸውን ለይተው የማቆየት ጥብቅ ግዴታ አለባቸው።

ይህ የመንግሥት ውሳኔ የተሰማው አንድ ጥናት አድራጊ ቡድን በቫይረሱ መያዛቸውን ካወቁ ሰዎች መካከል እራሳቸውን ለይተው ያቆዩት 18 በመቶ ያክሉ ብቻ ናቸው ማለቱን ተከትሎ ነው።

በቫይረሱ መያዛቸውን ያወቁ ወይም የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች ለ10 ቀናት፤ በግለሰቦችም ሆነ በብሔራዊ የጤና አገልግሎት ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳላቸው የተነገራቸው ሰዎች ደግሞ ለ14 ቀናት እራሳቸውን ለይተው ማቆየት ይኖርባቸዋል።

በዚህ ወቅት እንደ ምግብ እና መድኃኒት መግዛት ለመሳሰሉ መሠረታዊ ለሚባሉ ጉዳዮች እንኳን ቢሆን ከጤና ወሸባ ወጥተው መንቀሳቀስ አልተፈቀደላቸውም።

ከዛሬ ጀምሮ ይህን ጥብቅ መመርያ ጥሰው በሚገኙት ላይ እንደየጥፋታቸው ከ1ሺህ እስከ 10ሺህ ፓውንድ መቀጫ ይላለፍባቸዋል።

ፖሊስም የሚደርሱትን መረጃዎችን በመጠቀም ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ያደርጋል ሲል መንግሥት አስታውቋል።

በዚህ ምክንያት አነስተኛ ገቢ ኖሯቸው መሥራት ያልቻሉ እንዲሁም እራሳቸውን መለየት ስለሚኖርባቸው መሥራት ያልቻሉ ሰዎች የ500 ፓውንድ ድጎማ ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።

ከዚህ ቀደም የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ተከትሎ በእንግሊዝ እስከ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከመንግሥት ድጋፍ አግኝተው ነበር።

የአገር ውስጥ ሚንስትሩ ፕሪቲ ፓቴል ‹መንግሥት ያስቀመጣቸው ገደቦች ግልጽ ናቸው…› ካሉ በኋላ በብዙኃኑ ሕግ አክባሪ ዜጎች ጥረት የተገኘውን ውጤት ወደኋላ በሚጎትቱ ዳተኛ ሰዎች ላይ ቅጣት እንደሚጣል ተናግረዋል።

የጤና ሚንስትሩ ማት ሃንኮክ በበኩላቸው አሁንም እንደ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ የሚቀጥል ከሆነ ጠንከር ያሉ ክልከላዎችን እንደሚጥሉ አስታውቀዋል።

ከነሐሴ ወር ወዲህ በእንግሊዝ እና ዌልስ የኮሮናቫይረስ ሕግጋቶችን የተላለፉ 19ሺህ ሰዎች ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ለጤና ባለሙያዎች እራሳቸው ከበሽታው የሚከላከሉበትን የሕክምና ቁሳቁሳ ባልተቋረጠ መልኩ ማቅረብ እንደሚጀምር አስታውቋል።

ጓንት፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እና ጋዋን የመሳሰሉ መገልገያ ቁሶች ለአራት ወራት ሊዘልቅ የሚችል ክምችት መኖሩን ተገልጿል።