ቤላሩሱ ፡ ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ ከቪላድሚር ፑቲን ፖሊሶችን ሊዋሱ ነው

ታትሟል

ከምርጫ በኋላ ተቃውሞ የገጠማቸው ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ ወደ ሞስኮ በመሄድ የጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች ድጋፍ ከሩሲያ እንደሚጠይቁ ተነገረ።

ከሩሲያ የቤላሩስ ዋና ከተማ ሚንስክ ትናንትና እሑድ በከፍተኛ ተቃውሞ ስትናጥ ነበር የዋለችው፡፡

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿ አደባባይ ነው የዋሉት፡፡

ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ደግሞ ምስጢራዊ ደኅንነቶቻቸውን አሰማርተው ሰልፈኞችን እያሳፈኑ ከባድ የሥራ ቀን አሳልፈዋል፡፡

አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ሥልጣን አልጠገብኩም እያሉ ያሉት ከ26 ዓመታት በኋላ ነው፡፡

በዘመናዊ ታሪክ በአውሮፓ ምድር እንደ ሉካሼንኮ ለረዥም ዘመን በሥልጣን መንበሩ የተቀመጠ መሪ የለም፡፡

ሉካሼንኮ አሁን ቭላድሚር ፑትንን ለማግኘት ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ ይህ ዜና ሲጠናቀር ወደ ክሬምሊን በጉዞ ላይ ናቸው፡፡

በቤላሩስ አመጽ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ቪላድሚር ፑቲን ከሉካሼንኮ ጋር በአካል ሲገናኙ ለመጀመርያ ጊዜ ነው የሚሆነው፡፡

ሆኖም ግን ሁለቱ መሪዎች በየጊዜው ይደዋወላሉ፡፡

ባለፈው ምርጫ ሉካሼንኮ በከፍተኛ ውጤት አሸንፊያለሁ ሲሉ ያወጁ ሲሆን ሕዝባቸው ግን "እርስዎ ሰውዬ ማጭበርበር አይሰለችዎትም ወይ?" ብሏቸዋል፡፡

ቪላድሚር ፑቲን ግን እኔ የቤላሩስ ሕጋዊ መሪ ሆኖ የማውቀው አሌክሳንደር ሉካሼንኮን ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ፑቲን ለሉካሼንኮ "ሕዝቡ እየረበሸ ካስቸገረህም አመጽ የሚያዳፍኑ ፖሊሶችን እናውስሀለው" ሲሉ ቃል ገብተውላቸዋል፡፡

ቪላድሚር ፑቲንና አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የሚገናኙት በክሬምሊን ሳይሆን በጥቁር ባሕር ዳርቻ መዝናኛ ከተማ ሶቺ ውስጥ እንደሚሆን መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

የአሌክሳንድ ሉካሼንኮ አፋኝ ፖሊስ አመጽ ይመራሉ ያላቸውን በርካታ ሴቶች እያፈነ ታርጋ ቁጥር በሌላቸው ጥቁር ሚኒባስ መኪናዎች አፍኖ ሲወስድ ነበር፡፡

በዚህ መንገድ 400 ነውጠኞችን ማፈኑን መንግሥታቸው ይፋ አድርጓል፡፡

አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ሰልፈኞቹን በርቱ የሚሏቸው ምዕራባዊያን ስለሆኑ ሩሲያ ልክ ታስገባቸዋለች ሲሉ ይዝታሉ፡፡

አንድ ሉአላዊት አገር ከሌላ አገር ፖሊስ ተውሳ አመጽ ስታዳፍን ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡

ሩሲያ በሉካሼንኮ ላይ የተነሱትን ተቃውሞች በቅርብ ስትከታተል ቆይታለች፡፡

ሉካሼንኮ አመጹን የሚቆጣጠሩላቸውን ፖሊሶች ከሩሲያ መቼ እንደሚያስገቡ የታወቀ ነገር የለም፡፡

ፖለቲካ ተንታኞች ግን ሩሲያ ከሉካሼንኮ ጋር በቅርብ እየሰራች እንደሆነ ፊት ለፊት ብታሳይም ነገር ግን ከጀርባ የሷን ፍላጎት የሚያስፈጽሙ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው አመራሮችን ለማምጣት እየሰራች ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፡፡

ይህ የፖለቲከኞች ትንታኔ እውነት ከሆነ 26 ዓመት ቤላሩስን ጸጥ ረጭ አድርገው የመሩት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ሩሲያ የሄዱት መጦርያቸውን ለማመቻት እንጂ ፖሊስ ለመዋስ ላይሆን ይችላል፡፡