"የኤምባሲ ሠራተኞችን ደህንነት አደጋ ላይ መጣል ወንጀል ነው" የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና

ታትሟል

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ 'የኤምባሲ ሠራተኞችን ደህንነት አደጋ ላይ መጣል 'ተራ ወንጀል ነው' ብለዋል።

ከሰሞኑ ለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለተቃውሞ በተሰበሰቡ ሰልፈኞች የአገሪቱ ባንዲራ እንዲወርድ መደረጉና በኤምባሲው ሠራተኛ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።

«በቪዬና ኮንቬንሽን መሠረት የኤምባሲዎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት በዋናነት የአስተናጋጁ ሃገር ነው» ብለዋል ቃል አቀባዩ።

«ችግር ተፈጥሮባቸዋል ከተባሉ ኤምባሲዎች አምባሳደሮች ጋር ተግባብተናል፤ አስፈላጊውን ነገር እንደሚያደርጉም ቃል ገብተውልናል» ሲሉ ከዲፕሎማቶች ጋር ውይይት እንዳደረጉ ቃል አቀባዩ አሳውቀዋል።

አምባሳደር ዲና፤ ዜጎች በየትኛውም ሃገር ሆነው ተቃውሞ የማድረግ መብት አላቸው ይላሉ።

«ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፤ በፅሑፍ ሐሳብን ማቅረብ ወዘተ. . . ነገር ግን ከዚያ ባለፈ የኤምባሲዎችንና ዲፕሎቶችን ደህንነት 'ትሬትን' [አደጋ ላይ መጣል] ተራ ወንጀል ነው። የዲሞክራሲ መብት መገለጫ አይደለም።»

ቃል አቀባዩ ከለውጡ ጋር ተያይዞ «በሠለጠነ መንገድ ተቃውሞ መግለፅ ይቻላል፤ ይህ የመንግሥት ፅኑ አቋም ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለንደን ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባጋጠመው ክስተት አዲስ አበባ ውስጥ ላሉ የብሪታኒያ ኤምባሲ ከፍተኛ ባለስልጣን በይፋ ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል።

አምባሳደር ሬድዋን ኤምባሲው ላይ ስለተከሰተው ነገር በኢትዮጵያ የታላቋ ብሪታኒያና የዩናይትድ ኪንግደም ቻርጅ ዲ አፌር ለሆኑት አሌክስ ካሜሩን ነው ቅሬታቸውን ያቀረቡት።

በአረብ ሃገራት ያሉ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ጉዳይ

አምባሳደር ዲና በአረብ ሃገራት በስደት ላይ ያሉ ኢትዮጵያንን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ትላንት [ሐሙስ] ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ያወጣውን መግለጫ ዋቢ በማድረግ መንግሥት ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ወራት 3500 ዜጎች ወደ ሃገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉንም ቃል አቀባዩ አውስተዋል።

ቃል አቀባዩ በተደጋጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውጭ ሃገር ሲመለሱ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን በቻርተር አውሮፕላን ሁላ ወደ ሃገር ቤት እየመለሱ መሆኑ የመንግሥትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከሰሞኑ የተለያዩ የመብት ተሟጋቾች ቡድኖች ሳዑዲ አራቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያ ሰቆቃ በተሞላበት መንገድ ነው በስደተኛ ካምፖች ውስጥ የሚኖሩት የሚል ዘገባ አውጥተው የኢትዮጵያ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ አልወሰደም ሲሉ ወቅሰዋል።

ቃል አቀባዩ ግን መንግሥት ስደተኞቹን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።