ቤላሩስ፡ ፑቲን ቤላሩስን ከውጭ ሃገር ወረራ ለመከላከል 'ቃል ገቡ'

የፎቶው ባለመብት, EPA
የቤላሩስ ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ሩስያ ሃገራቸውን ከውጭ ሃገር ወረራ ለመከላከል ቃል መግባቷን ተናገሩ።
ፕሬዝደንቱ፤ ኔቶ በጎረቤት ሃገራት ፖላንድና ሉቱዋኒያ ወታደራዊ ልምምድ እያደረገ መሆኑ እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል።
ሉካሼንኮ ከቀናት በፊት የተከናወነውን ምርጫ አሸንፍያለሁ ማለታቸውን ተከትሎ በርካታ ቤላሩሳውያን አደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን እያሰሙ ነው።
ቅዳሜ ማለት በሺዎች የሚዎጠሩ ሰዎች የሃገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ፊት ቆመው ጣቢያው ተቃውሟቸውን እንዲያሰማላቸው ሲጠይቁ ታይተዋል።
ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ምርጫውን በሰፊ ውጤት አሸንፍያለሁ ቢሉም በርካቶች ግን ምርጫው ተጭበርብሯል ይላሉ።
የሃገሪቱ ማዕከላዊ የምርጫ ኮሚሽን፤ በአውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1994 ጀምሮ ሥልጣን ላይ ያሉት ሉካሼንኮ 80 በመቶ ድምፅ አግኝተዋል፤ ተቀናቃኛቸው ስቬትላና ቲካኖቭስካያ ደግሞ 10 በመቶ ድምፅ ነው ያገኙት ይላል።
ተቃዋሚዋ፤ 'ምርጫው ተጨበርብሯል። እኔ ያገኘሁት ድምፅ ከ60 እስከ 70 በመቶ ነው' ሲሉ ይሞግታሉ።
ተቃውሞ የበረታባቸው ፕሬዝደንት ሉካሼንኮ የሩስያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን እንዲተባበራቸው ተማፅነዋል።
እንደ ሉካሼንኮ ከሆነ ፕሬዝደንት ፑቲን ቤላሩስ ላይ ማንኛውም የውጭ ጥቃት ቢሰነዘር እርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
ሉካሼንኮ ይህን ያሉት የአውሮፓ ሕብረት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የቤላሩስ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ለመጣል ከተስማሙ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
አሜሪካም ምርጫው 'ነፃና ፍትሃዊ' አይደለም ትላለች።
ጎረቤት ሃገራት የሆኑት ላቲቪያ ሉቱዋኒያ፤ ቤላሩስ ውስጥ ያለውን አለመስማማት በውይይት ለመፍታት ሞክረው ካልተሳካላቸው የሉካሼንኮ መንግሥት ላይ ማዕቀብ ለመጣል ዝተው ነበር።
ከምርጫው በፊት ለደህነነታቸው በሚል ልጆቻቸውን ወደ ጎረቤት ሃገር ያሸሹት ተቃዋሚዋ ስቬትላና የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉ በይፋ ካወጁ በኋላ እሳቸውም ወደ ሉቱዋኒያ መሄዳቸው አይዘነጋም።
ከምርጫው በኋላ በተነሳ ግጭት ሳቢያ እስካሁን ቢያንስ 6 ሺህ 700 ሰዎች ታስረዋል። በርካቶች በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ስቃይ እየደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ዋነኛዋ ተቀናቃኝ ስቬትላና ከትላንት በስቲያ [አርብ] ሰላማዊ ተቃውሞች እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ የቤላሩስ ዋና ከተማ ሚንስክ መንገዶች በሰልፈኞች ተጥለቅልቃለች።
100 ገደማ የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ሠራተኞች ከዋና መሥሪያ ቤቱ ወጥተው ተቃዋሚዎችን ተቀላቅለዋል። በርካቶች ደግሞ በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀዋል።
የሃገሪቱ ቴሌቪዝን ጣቢያ የገዥውን መንግሥትን ድምፅ ብቻ ነው የሚያንፀባርቀው የተቃዋሚዎችን ድምፅ አላሰማም ተበሎ ሲወቀስ ነበር።
በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች 'ይልቀቁ' የሚል መፈክር አንግበው ሉካሼንኮ ከሥልጣን እንዲወርዱ እየጠየቁ ነው።













