በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሰከረ ወታደር 13 ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ ተቃውሞ ተነሳ

የፎቶው ባለመብት, Jean Chung
በዲሞክራቲክ ኮንጎ 13 ሰዎችን የገደለው ወታደር እየተፈለገ እንደሆነ የአገሪቱ ጦር አስታወቀ።
ይህ የተፈፀመው በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ዩቪራ ሲሆን ከተገደሉትም መካከል ሴቶችና ህፃናት ይገኙበታል።
ጥቃቱን የፈጸመው ወታደር ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮልም ጠጥቶ ሰክሮ ነበር ተብሏል።
ወታደሩ በትናንትናው ሐሙስ ሐምሌ 23/2012 ዓ.ም ምሽት አካባቢ ነው ተኩሶ ሰዎቹን የገደላቸው።
ይህንንም ተከትሎ በግዛቲቱ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሷል። በርካቶችም የአካካቢው ጦር ኃላፊ እንዲቀየርም እየጠየቁ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በዚህ በወታደሩ ጥቃት ለሞቱና ለቆሰሉ ቤተሰቦችም መንግሥት ካሳ እንዲከፍልም እየጠየቁ ነው።
በግዛቲቱ ከሰሞኑም ከፍተኛ ጎርፍ ተከስቶ አርባ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በሺህዎች የሚቆቱ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ከዚህ በተጨማሪ ታጣቂዎችም በርካታ ሰዎችን ገድለዋል።
በተፈጥሯዊ አደጋና በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት በርካቶች የሞቱባት ግዛት ከሃዘኗ ሳታገግም በሰከረው ወታደር በተከፈተው ተኩስ 13 ሰዎች መገደላቸው የአካባቢውን ነዋሪዎች ሐዘን እጥፍ ድርብ አድርጎታል።
በማዕከላዊ አፍሪካ ውስጥ የምትገኘው በማዕድን ሐብቷ የበለጸገችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተለያዩ ግዛቶቿ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አማጺያንን ለመቆጣጠር ሠራዊቷን አሰማርታ ትገኛለች።












