ከኢትዮጵያ ለጂቡቲ ተላልፎ የተሰጠው አብራሪ በረሃብ አድማ ላይ ነው ተባለ

ታትሟል

ኢትዮጵያ ውስጥ ተይዞ ለጂቡቲ ተላልፎ የተሰጠውና በአገር ክህደት የተከሰሰው ጂቡቲያዊው የአየር ኃይል አውሮፕላን አብራሪ እስር ላይ እያለ ለሁለተኛ ጊዜ የረሃብ አድማ እያደረገ መሆኑ ተነገረ።

በእስር ላይ የሚገኘው የፉዐድ ዩሱፍ ጠበቃ ለፈረንሳይ ሬዲዮ እንደገለጹት የአብራሪው የጤና ሁኔታ ችግር ላይ ቢሆንም ምግብ ለመብላት ፈቃደኛ አይደለም።

በተጨማሪም ላለበት የጤና ችግር ህክምና እንዲያገኝ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ልመረዝ እችላሁ በሚል ምክንያት ህክምና ለማግኘት እንደማይፈልግ ገልጿል ተብለዋል።

አብራሪው ወታደራዊ አውሮፕላን ይዞ ከአገር ለመውጣት ሙከራ አድርጓል በሚል የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጎታል።

የጂቡቲ ወታደራዊ ባለስልጣናትን በሙስና በመክሰስ ባለፈው መጋቢት ወር ወደ ኢትዮጵያ በመሸሽ ጥገኝነት ለማግኘት ቢሞክርም ተይዞ በሚያዚያ ወር ላይ ለአገሩ መንግሥት ተላልፎ መሰጠቱ ተነግሯል።

ፉዐድ ለጂቡቲ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ በአገር ክህደት ተከሶ በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን ቀደም ሲል ያለበት እስር ቤት ኃላፊዎች በአግባቡ እንዳልያዙት የከሰሰ ሲሆን ቤተሰቦቹም መንግሥት እያንገላታቸው መሆኑን በመግለጽ ተናግረው ነበር።

ነገር ግን የጂቡቲ መንግሥት የቀረበበትን ክስ ሐሰት መሆኑን በመግለጽ አስተባብሏል።

ይህንን ተከትሎም የሰብአዊ መብት ተከራካሪው ድርጅት ሂማን ራይትስ ዋች የጂቡቲ መንግሥት የቀረበበትን ክስ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

አብራሪው ሰቆቃ እንደተፈጸመበት የሚገልጽ ቪዲዮ ከእስር ቤት ሾልኮ ከወጣ በኋላ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ጂቡቲ ውስጥ ድርጊቱን የሚቃወሙ ዜጎች አደባባይ ወጥተው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የጂቡቲ አምባሳደር ሞሐመድ ኢድሪስ ፋራህ ከዚህ ቀደም ለሮይተርስ ፓይለቱ የታየዘው ሚያዝያ ወር ላይ አዲስ አበባ ውስጥ እንደሆነ ገልጸው፤ ወደ ኢትዮጵያ የሸሸው አውሮፕላን ይዞ ወደ ኤርትራ ለመጓዝ ሙከራ ካደረገ በኋላ እንደሆነ አመልክተው ነበር።