ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በናይጄሪያ በየአምስት ሰዓቱ አንዲት ሴት ትደፈራለች
ናይጄሪያ ለሴቶች የምትሆን አገር አትመስልም። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ጾታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል።
ለምሳሌ ካለፈው መስከረም እስከ ግንቦት ድረስ ብቻ የተመዘገበ የጥቃት ሰነድ ብናገላብጥ በዚያች አገር 717 ሴቶች ተደፍረዋል። ይህ ማለት በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ በየአምስት ሰዓቱ አንዲት ሴት ስትደፈር ነበር እንደማለት ነው።
የፖሊስ አለቃ መሐመድ አዳሙ ይህን አስቀያሚ ድርጊት ለማቆም ናይጄሪያዊያን እንዲረባረቡ ጥሪ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ሙሐመድ ቡሃሪን በጉዳዩ ዙርያ ካነጋገሯቸው በኋላ በአቡጃ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የፖሊስ አዛዥ ከሴቶች መደፈር ጋር ተያይዞ 799 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። 631 ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ነገር ግን የፖሊስ አዛዡ በምን ያህሉ ላይ ፍርድ መሰጠቱን፣ ምን ያህሉስ ጥፋተኛ ተብለው ዘብጥያ መውረዳቸውን አልተናገሩም።
በናይጄሪያ ደፋሪዎች በቁጥጥር ሥር ቢውሉም ጥፋተኛ አድርጎ በፍርድ ቤት ማስወሰን ቀላል ጉዳይ እንዳልሆነ ይነገራል።
በቅርብ ጊዜ አንዲት ሴት በኃይል ከተደፈረች በኋላ የመገደሏ ዜና ባለፉት ሳምንታት በናይጄሪያ ቁጣን የቀሰቀሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር። በናይጄሪያ ከተሞችም በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄደዋል።
የፖሊስ አዛዡ እንደሚሉት ችግሩ የአስተሳሰብም ስለሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ስልጠናን የመስጠት ሐሳብ ተይዟል።
ከዚህ ባሻገር አጥፊዎቹን በደንብ ለመቅጣት መረጃ አሰባሰብ ላይ እና ክስ አመሰራረት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።