ፖላንድ ለአጭር ጊዜ ቼክ ሪፐብሊክን "በስህተት ወራት" እንደነበር አመነች

ታትሟል

ፖላንድ በባለፈው ወር ለአጭር ጊዜ ቼክ ሪፐብሊክን ወራት እንደነበርና የመከላከያ ሚኒስትሩም " ባለመግባባትና በስህተት" የተፈጠረ ነው ብለውታል።

የኮሮናቫይረስን መዛመትን ለመግታት በሚል የፖላንድ ወታደሮች ዜጎች ከሃገር እንዳይወጡና እንዳይገቡ በድንበር ቦታዎች ላይ ተሰማርተው ነበር።

ወታደሮቹ ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር የሚያዋስናቸውን ድንበር አልፈው በመግባት ቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ የሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያንም ተቆጣጥረው ነበር።

ወታደሮቹ ለቀናትም በቦታው ከመቆየት በተጨማሪ ቦታውን ለመጎብኘት የሚፈልጉ የቼክ ዜጎችንም ሲከለክሉ ነበር።

የቼል ባለስልጣናትም የፖላንድ መንግሥትን በማሳወቅ ጣልቃ ሊገቡ ችለዋል።

ሁኔታው የተከሰተው በሰሜን ምስራቃዊ ግዛት ሞራቪያ የምትባል ቦታ ሲሆን በቦታውም ታሪካዊ የሆነችው ስፍራ ሲለሲያ ትገኛለች።

ሲለሲያ በሁለቱም ሃገራት በኩል ትገኛለቸቭ።

ፖላንድ ክስተቱን ስህተት ቢልም የቼክ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ መንግሥታዊ የሆነ ገለፃ እፈልጋለሁ ብላለች።

ምን ተፈጠረ?

መጀመሪያ ይሄ ዜና የወጣው በቀጠናው ባለው ዴኒክ በሚባል ጋዜጣ ነበር።

አንድ መሃንዲስ የቤተክርስቲያኑን እደሳ ለማየትና ፎቶ ለማንሳትም ሲሞክር መሳሪያ የታጠቁ የፖላንድ ወታደሮች ከለከሉት።

ወታደሮቹ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚያመራው መንገድንም ዘግተውት ነበር።

ዴኒክ ጋዜጣ ለሰውየው ቃለ መጠይቅ ከማድረክ በተጨማሪ በአካባቢው ያለውን ነገር የሚያሳይ ፎቶ ይዞ ወጣ። ፎቶውም መሃንዲሱ ያለውን ነገር የሚያረጋግጥ ነበር።

ቤተክርስቲያኗ በቼክ ሪፐብሊክም ሰላሳ ሜትር ግዛት ውስጥ ይገኛል። የሁለቱ ሃገራትን የሚያዋስናቸው ድንበር በውሃ የተከበበ ነው።

ዴኒክ ባወጣው ፅሁፍ ላይ የፖላንድ ወታደሮች የፖላንድን የውሃ ስርጥ እንደተቆጣጠሩና ባልታወቀ ምክንያትም ወደ ቼክ ሪፐብሊክ በመግባት ግዛቷንም ወረዋል ብሏል።

ግዛቷ በፖላንድ ወታደሮች ስር ለምን ያህል እንደቆየች አልተገለፀም።

መሃንዲሱ በፖላንድ ወታደሮች እንዳልገባ ተከልክያለሁ ያለው ሐሙስ ግንቦት 20፣ 2012 ዓ.ም እንደነበርና በቀጣዮቹም በነበሩት ቅዳሜና እሁድ በነበሩትም ቀናት ወታደሮቹ እንዳልለቀቁ ጋዜጣው አስነብቧል።

በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራ "የመሬት ጓደኞች" የተሰኘ እንቅስቃሴም በቦታው ላይ ስብሰባ ለማካሄድ አቅዶ ነበር። የእንቅስቃሴው አንደኛው አስተባባሪ ኢቮ ዶኮፒል እንደተናገሩት ቡድኑ ቤተክርስቲያኗን ለመጎብኘት እንዲሁም ፎቶዎች ለማንሳት ቢፈልጉም በማይሆን ሁኔታ ወታደሮቹ እንደመለሷቸው ተናግረዋል።

"የውጭ ሃገር መለዮ የለበሰና መሳሪያ የታጠቀ ወታደር ተቆጥቶ ትእዛዝ ይሰጠኝ ጀመር። ሁኔታውም ያስፈራል" ማለቱንም ዴኒክ ጋዜጣ አስተባባሪውን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

"በአቅራቢያውም አስር ሜትር ያህል እንድጠጋም አልፈቀዱልኝም" ብሏል።

የአካባቢው የቼክ ሪፐብሊክ የፖሊስ ኃይልም ተጠርቶ ወታደሮቹ አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱም መጠየቃቸው ተዘግቧል።

"በድንበሩ ላይ ወታደሮች የተሰማሩት በስህተት ነው፤ ባለመግባበት የተፈጠረ ነው አውቀን ያደረግነው አይደለም። ስህተት መፈጠሩም እንደታወቀ ችግሩን ፈትተነዋል" በማለት የፖላንድ መከላከያ ሚኒስትር ለሲኤንኤን ተናግረዋል።