ትራምፕ ሩስያ ወደ ቡድን 7 ትመለስ ቢሉም አባል አገራቱ ተቃውመዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩስያ፤ ወደ ቡድን 7 (G7) እንድትመለስ ቢፈልጉም ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳ ተቃውመዋል።
ትራምፕ፤ በዚህ ወር ሊካሄድ እቅድ ተይዞለት የነበረውን የቡድን 7 ስብሰባ ለመስከረም አስተላልፈዋል። ባለፈው እሁድ በሰጡት መግለጫ የቡድን ሰባት አገራት ሩስያን ወደ ቡድኑ መልሰው እንዲቀላቅሉ ጠይቀዋል። ሩስያን ወደ ቡድኑ ለመመለስ እንዳቀዱም ለፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን በስልክ ነግረዋል።
አሜሪካ በምታስተናግደው የዘንድሮ ስብሰባ፤ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጃፓንና ዩኬ ይገኛሉ። ስለትብብር ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ሆኖም ግን የካናዳና ዩኬ መሪዎች የሩስያን ወደ ቡድኑ መመለስ እንደማይቀበሉ እሁድ ተናግረዋል።
ሩስያ ቀድሞ ቡድን ስምንት (G8) ተብሎ ከሚጠራው የአገራት ስብስብ የተባረረችው ክሬሚያን የግዛቷ አካል በማድረጓ ነበር። ከተባረረች ስድስት ዓመት ሆኗታል።
“ሩስያ ከጂ7 የተባረረችው ክሬሚያን ስለወረረች ነው። ዓለም አቀፍ ሕግጋት መጣስ በመቀጠሏ ነው ከቡድኑ ውጪ የተደረገችው። ተመልሳም አትገባም” ብለዋል የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ።
የዩኬው ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ቃል አቀባይ፤ ሩስያ ወደ ቡድኑ ትግባ የሚል ሀሳብ ቢቀርብ፤ ድምጽን በድምጽ በመሻር መብታቸው እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል።
“ሩስያ ነውጠኛና ሰላም የሚያውኩ ድርጊቶችን እስካላቆመች ወደ ቡድኑ እንድትመለስ አንደግፍም” ብለዋል።
ከሦስት ዓመታት በፊት የቀድሞ የሩስያ ሰላይ በእንግሊዝ መገደሉን ተከትሎ፤ የዩናይትድ ኪንግደምና ሩስያ ግንኙነት ሻክሯል።
ዩኬ እና ካናዳ ፑቲን የቡድን ሰባትን ስብሰባ በአሜሪካ መታደማቸውን አልተቃወሙም። ከዚህ በፊት የቡድኑ አባል ያልሆኑ አገራት ስብሰባ ተሳትፈው ያውቃሉ።
የቡድኑ አባል አገራት ሩስያ እንድትመለስ አንፈልግም ቢሉም፤ ትራምፕ በተደጋጋሚ ለሩስያ ድጋፋቸውን አሳይተዋል።
እአአ 2018 ላይ በተካሄደ የቡድን 7 ስብሰባ “ሩስያ ብትመለስ ጠቃሚ ትሆናለች” ብለው ነበር።
ባለፈው እሁድ በሰጡት መግለጫም ይህንኑ አቋም መልሰው አስተጋብተዋል። “ቡድኑ ዓለም ላይ እየተከናወነ ያለውን ነገር አይወክልም” ሲሉም፤ ሩስያ፣ ደቡብ ኮርያ፣ አውስትራሊያ እና ሕንድ ወደ ቡድኑ ይቀላቀሉ ብለዋል።
የደቡብ ኮርያ እንዲሁም የአውስትራሊያ መሪዎች አሜሪካ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ባለፈው ሳምንት የጀርመኗ መራሔተ መንግሥት አንጌላ መርክል፤ በኮሮናቫይረስ ስጋት የቡድኑን ስብሰባ በአካል እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል።
የተሻለ ምጣኔ ሀብትን መሠረት አድርገው የተሰባሰቡት ሰባት አገራት፤ በየዓመቱ እየተገናኙ ስለ ዓለም አቀፍ አስተዳደር፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የደህንነትና የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ይወያያሉ።
አባላቱ መርሃችን የሚሉት፤ ነፃነት፣ የሰብዓዊ መብት መከበር፣ ዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነትና ዘላቂነት ያለው እድገትን ነው።












