ታጣቂው ካናዳ ውስጥ ቢያንስ 16 ሰዎችን ገደለ

የፎቶው ባለመብት, earthshod_kuunda
ካናዳ ውስጥ የፖሊስ የደንብ ልብስ የታጠቀ አንድ ግለሰብ አንዲት የፖሊስ መኮንን ጨምሮ 16 ሰዎችን መግደሉ ተሰምቷል።
ግድያው በካናዳ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የጅምላ ግድያ ነው ተብሏል።
በሃገሪቱ አቆጣጠር ቅዳሜ ምሽት 4 ሰዓት ገደማ የተጀመረው በፖሊስና በሰውዬው መካከል የተኩስ ልውውጥና የመኪና እሽቅድምድም ለ12 ሰዓታት ዘልቋል።
ፖሊስ ግሰለቡ ኖቫ ስኮሺያ በተባለችው ከተማ በተለያዩ ቦታዎች እየዞረ ሰዎችን በጥይት ገድሏል ሲል ዘግቧል። ግለሰቡ ከፖሊስ ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ መገደሉ ተዘግቧል።
ሰውዬው የፖሊስ መኪና እየነዳ ነበር የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
ፖሊስ የተኩስ ድምፅ እየተሰማ ነው የሚል ጥቆማ ደርሶት ወደ ቦታው ሲደርስ በርካታ ሰዎች ተጎድተው ቢታዩም ሰውዬው ግን በጊዜው አልተገኘም ነበር ተብሏል።
ተጠርጣሪው ከቆይታ በኋላ ማንነቱ ሲጣራ ጋብርኤል ዎርትማን የተሰኘ የ51 ዓመት የአካባቢው ነዋሪና ሁለት ትላልቅ ሕንፃዎች ያሉት ሆኖ ተገኝቷል።
ፖሊስ የተኩስ ድምፅ ጥሪ ሲደርሰው ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ጠቁሞ ነበር። የአካባቢው ነዋሪዎች ግለሰቡ የገዛ መኖሪያውንና የሌሎች ሰዎችን ቤት በእሣት ማያያዝ ከጀመረ በኋላ ሰዎች መሸሽ ሲጀምሩ ነው የተኮሰባቸው ሲሉ የዓይን ምስክርነት ሰጥተዋል።
ከዚያ ፖሊስ ግለሰቡን ለ4 ሰዓታት ያክል ሲያስስ ቆይቷል።
የሟቾች ቁጥር 16 ነው ይባል ሙሉ በመሉ በግድያው ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቀጥር አልታወቀም። ከሟቾች መካከል የ23 ዓመቷ የአካባቢው ፖሊስ አባል የሆነችው ኮንስታብል ሃይዲ ስቴቨንሰን ትገኝበታለች።
የተጠርጣሪው ጎረቤቶች ሰውዬውን በጣም ትርፋማ የሆነ የጥርስ ክሊኒክ ያለውና በሥፍራው ሠርቶ ማደር የሚፈልግ ነበር ሲሉ ገልፀውታል። ፖሊስም ሰውዬው የተረጋጋ ሕይወት የነበረው እንደሆነ ነው የምናውቀው ይላል። ሟቾቹም ምንም የሚያገናኘቸው ነገር የለም ተብሏል።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስር ጀስቱን ትሩዶ 'በጣም የሚረብሽ ክስተት' ሲሉ ሁኔታውን ገልፀውታል።
ካናዳ ውስጥ የታጠቁ ሰዎች የግድያ ወንጀል ሲፈፀሙ መስማት የተለመደ አይደለም። እንደ ጎረቤት ሃገር አሜሪካ ካናዳ ውስጥ የጦር መሣሪያ መታጠቅ ቀላል አይደለም።












