ኮሮናቫይረስ ያጠላበት የዛሬው ፀሎተ ሐሙስ እንዴት እየተከበረ ነው?

ታትሟል

ዛሬ ፀሎተ ሐሙስ ነው። ለወትሮው እለቱን ምዕመናን ቤተ ክርስትያን በመሄድ በፀሎት ያሳልፉ ነበር። ዘንድሮ ግን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሲባል ምዕመናን ቤተ ክርስቲያን እንዳይሄዱና ሥነ ሥርዓቱን ቤት ሆነው በተለያዩ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዲከታተሉ ታውጇል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ አገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ኃላፊ መላከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወልደየሱስ ሰይፉ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ መንግሥት እንዲሁም ቅዱስ ሲኖዶሱ ባወጣው መመሪያ መመሰረት ምዕመናን ከቤታቸው ሆነው የፀሎተ ሐሙስ ሥነ ሥርዓትን እንዲከታተሉ ተደርጓል።

"በአዲስ አበባ በሁሉም አድባራት መመሪያው ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል። ኅብረተሰቡ በየቤቱ ተቀምጦ የቀጥታ ስርጭቱን እንዲከታተልም ተደርጓል" ይላሉ።

በየቤተክርስቲያኑ ያለውን ሥርዓተ ቅዳሴ፣ ግብረ ሕማማ ንባብ እና አጠቃላይ አገልግሎቱ በተለያዩ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በቀጥታ እየተላለፈ ነው። የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ በባላገሩ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጣቢያዎች ላይ እየታየ ሲሆን፤ የቦሌ መድኃኔዓለም አገልግሎት በፋና ቴሌቭዥን እየተሰራጩ ይገኛሉ።

"አልፎ ተርፎም መብራት በጠፋባቸው አካባቢዎች መብራት እንዲለቀቅም የሚመለከተውን አካል ጠይቀናል" ሲሉ መላከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወልደየሱስ ሰይፉ ተናግረዋል።

መመሪያውን ለማስፈጸም በየቤተ ክርስቲያኑ የጸጥታ አካላት እንደተገኙ ገልጸውም፤ "ኅብረተሰቡ ለራሱ መሆኑን አውቆ እየተባበረ ነው" ብለዋል።

በአዲስ አበባ በአስሩም ክፍለ ከተሞች በቤተ ክርስቲያን የተገኙ ጥቂት ምዕመናን ማኅበራዊ ርቀት ጠብቀው እንዲቆሙ በማድረግ ረገድ በጎ ፍቃደኛ የሰንበት ተማሪዎች እያስተባበሩ እንደሚገኙም አክለዋል።

እሳቸው በሚገኙበት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የተገኙ ጥቂት ምዕመናን አንዳቸው ከሌላቸው ተገቢውን ርቀት እንደጠበቁም ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"ዛሬ ዋናው የሥጋ ወ ደሙ ሚስጥር የተፈጸመበት እለት ስለሆነ ሁሉም ቀሲሳን ይቆርቡ ነበር። አሁን ካለው ችግር የተነሳ ግን ቤተ ክርስትያን ያለ ሰው ብቻ እንጂ ማንም ሰው ከውጪ እንዲካፈል አልተደረገም። የበለጠ በበሽታው ተጠቂ እንዳይኮን በሚል ነው ይህ የተደረገው" ይላሉ።

በፀሎተ ሐሙስ የሚካሄደው እግር የማጠብ ሥነ ሥርዓት ነው። መላከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወልደየሱስ ሰይፉ፤ "በየቤተ ክርስቲያኑ ካሉ ጥቂት አባቶች ውጪ ንክኪ አይኖርም" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ "ምዕመናን በጉጉት በሚጠባበቁት የማጠቃለያው ሥርዓተ ቅዳሴና ቅዱስ ቁርባን ለመሳተፍ እንዳይከለከሉ" የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚንስትሩ እንደጻፉ ቢቢሲ ተረድቷል።

ፓትሪያርኩ በደብዳቤያቸው ዛሬ በጸሎተ ሐሙስ እና እሁድ በበዓለ ትንሣኤ ቆራቢዎች የሆኑ ምዕመናን የጤና ጥበቃ ሚንስቴር በሰጠው ምክር መሠረት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እንዲቆርቡ ክልከላው እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል።

ቢቢሲ ፓትሪያርኩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጻፉት ደብዳቤ የተሰጠ ምላሽ እንዳለ ከቤተ ክርስቲያኗ ለማረጋገጥ ጥረት ቢያደርግም ከዕለቱ ሥነ ሥርዓት በኋላ መልስ እንደሚሰጡን ያነጋገርናቸው ኃላፊዎች ነግረውናል።