በእስላም መቃብር በስህተት የተቀበረው ናይጀሪያዊ አስከሬን ተቆፍሮ ወጣ

ታትሟል

በናይጀሪያ አስከሬን ክፍል በተፈጠረ ስህተት በሙስሊሞች መካነ መቃብር የተቀበረው የክርስትና እምነት ተከታይ ግለሰብ አስከሬን ተቆፍሮ ወጥቷል።

ክስተቱ የተፈጠረው በሰሜናዊ ካኖ በምትገኘው ግዛት ውስጥ ሲሆን ለዚህም እንደ ምክንያትነት የተሰጠው በወቅቱ የሞቱ ሁለት ግለሰቦች መመሳሰል ነው ተብሏል።

የግዛቷ ኢማም አሚኑ አዳምም ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለተፈጠረው ውዥንብር ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ነው።

"የሟቹን አብዱላሂ ኦቢንዋን አስከሬን ለመለየት በሄድኩበት ወቅት 22 ቁጥር እንደሆነ ተነገረን። ሌላኛው ሟች ባሲል ኤጀንሲ በተመሳሳይ ወቅት ነው ያረፈው። ሁለቱም ወፈር ያሉ፣ ቁመታቸው መጠነኛ ነው" በማለት የአካላዊ ገፅታቸው መመሳሰል ስህተት እንደፈጠረባቸው ኢማሙ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የአስከሬን ክፍሉን አስተባባሪ በጠየቁበት ወቅት ለቀብር ሲያዘጋጁ ፂም እንደሚላጩ በነገሯቸው መሰረት ሟቹ አብዱላሂ ነው በማለት የባሲልን አስከሬን ወስደዋል።

የሌላኛው ሟች ባሲል ኤጀንሲ ቤተሰቦች መጥተው አስከሬኑን ለመውሰድ በሚሞክሩበት ወቅት ነው ስህተት እንደተፈጠረ የታወቀው። አስከሬኑን የት እንደሄደ ለማወቅ በሚጥሩበትም ወቅት በሙስሊም መቃብር ቦታ እንደተቀበረም ለመረዳት ችለዋል።

ምንም እንኳን ግለሰቡ ከተቀበረ ሳምንት ቢያልፈውም፤ ቤተሰቦቹ ከፍርድ ቤት ወረቀት በማምጣት መቃብሩ እንዲቆፈር በማድረግም አፅሙን ወስደዋል።

እስካሁን ድረስ የሌላኛው ሟች አብዱላሂ ኦቢንዋ አስከሬን ማግኘት አልተቻለም።

አስከሬኑ የነበረበት የአሚኑ ካኖ ሆስፒታል አስተዳደር በበኩላቸው ይህ ስህተት እንደተፈጠረ ለማወቅ ምርመራ መክፈታቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።