ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን የተከሰከሰውን አውሮፕላን የመረጃ ሳንዱቅ ለቦይንግም ሆነ ለአሜሪካ አልሰጥም አለች
ኢራን 176 ሰዎችን አሳፍሮ የተከሰከሰውን አውሮፕላን የበረራ መረጃዎች የያዘውን ጥቁር ሳንዱቅ ለአምራቹ ቦይንግም ሆነ ለአሜሪካ አሳልፌ አልሰጥም አለች።
ንብረትነቱ የዩክሬን የሆነው ቦይንግ 737-800 ከቴህራን አውሮፕላን ማረፊያ በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ነበር የተከሰከሰው።
በዓለም አቀፍ አቪየሽን ሕግ መሰረት ኢራን ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያት የሆነውን፤ ለማወቅ የሚደረገውን ምርመራ የመምራት መብት አላት።
አምራቾች በአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ምርመራው ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በጣም ጥቂት ባለሙያዎች ብቻ የመረጃ ሳንዱቁ ያዘውን የመረዳትና የማብራራት ብቃቱ አላቸው።
አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በኢራንና በአሜሪካ መካከል ያለው ውጥረት በተጋጋለበት ወቅት ነው።
ኢራን አውሮፕላኑ ከመከስከሱ ጥቂት ሰዓታት በፊት ኢራቅ በሚገኝ የአሜሪካ ወታደሮች መኖሪያ ሰፈር ላይ የሚሳዔል ድብደባ ያካሄደች ሲሆን፣ የአውሮፕላኑ መከስከስና የሚሳዔል ድብደባው የሚያገናኛቸው ነገር መኖር አለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።
እስከዛሬ በተለመደው አሰራር ከሆነ የቦይንግ አውሮፕላኖች አደጋ ሲገጥማቸው የአሜሪካ ብሔራዊ ትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ በአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ምርመራው ላይ ይሳተፍ ነበር።
ነገር ግን ቦርዱ አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት አገር ፈቃድ ማግኘትና የዚያን አገር ሕግ ማክበር ይኖርበታል።
በኢራን የወግ አጥባቂዎች ደጋፊ የሆነው ሜህር የተሰኘው መገናኛ ብዙኀን የኢራን ሲቪል አቪየሽን የበላይ ኃላፊ አለኪ አቤዳዝዳህን ጠቅሶ "የመረጃ ሳንዱቅን ለአውሮፕላኑ አምራችም ሆነ ለአሜሪካኖች አንሰጥም" ማለታቸውን ዘግቧል።
"አደጋው በኢራን አቪየሽን በኩል ምርመራ ይደረግበታል፤ ነገር ግን ዩክሬናውያን ሊገኙ ይችላሉ" ሲሉ ተናግረዋል።
አቤዳዝዳህ ጥቁሩ ሳንዱቅ ያዘውን መረጃ ለመተንተን የትኛዋ አገር እንደምትሳተፍ ያሉት ነገር የለም።
ቦይንግ "አስፈላጊ በሆነበት ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን" ያለ ሲሆን የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ አገራቸው በምርመራው ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት በማስታወቅ፣ የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ረብዑ ዕለት 176 ሰዎችን አሳፍሮ የተከሰከሰው አውሮፕላን ከኢራን ተነስቶ መድረሻውን ዩክሬን ኪየቭ ነበር ተብሏል።
የበረራ ቁጥር PS752 የሆነው ይህ አውሮፕላን በርካታ የኢራንና የካናዳ ዜግነት ያላቸው ተሳፋሪዎችን ጭኖ ነበር።
በቴህራን የሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ ለአውሮፕላኑ መከስከስ ሞተሩ ያጋጠመው የቴክኒክ ችግር ነው ብሎ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ከአደጋ መርማሪው በፊት የሚሰጥ ማንኛውም አስተያየት ይፋዊ መረጃ አይደለም ብሏል።
የኢራን አቪየሽን ኃላፊ አቤዳዝዳህ፤ "አሸባሪዎች" በአውሮፕላኑ መከስከስ ላይ ምንም ተሳትፎ የላቸውም ማለታቸውን ሜህር የተሰኘው መገናኛ ብዙኀን ዘግቧል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሜር ዜሌንስኪ ከይፋዊ የምርመራ ውጤት በፊት የሚኖርን "ተራ ግምት ወይም ስለአደጋው ያልተጣራና ያልተረረጋገጠ መላምት" በሚመለከት አስጠንቅቀዋል።
በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩት 82 ኢራናውያን፣ 63 ካናዳውያን፣ 11 ዩክሬናውያን፣ 10 ሲውዲናውያን፣ 4 አፍጋኒስታናውያን፣ 3 እንግሊዛውያን፣ 3 ጀርመኖች እና የበረራ ሠራተኞች መሆናቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቫዲም ፕሪስታኮ ገልፀዋል።
ከሞቱት መካከል አስራ አምስቱ ሕጻናት ናቸው።
የጀርመን መንግሥት ግን "በአሁኑ ሰዓት ጀርመናውያን በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ ተሳፍረው እንደነበር መረጃ የለንም" ሲል አስታውቋል።