ኢራን፤ ኢራቅ የሚገኝ የአሜሪካ ይዞታን በሚሳዔል ካጠቃች በኋላ የነዳጅ ዋጋ ንሯል

ታትሟል

ኢራን፤ ኢራቅ ውስጥ የሚገኝ የአሜሪካ ወታደሮች መጠለያን በሚሳዔል ካጠቃች በኋላ የነዳጅ ዋጋ መናሩ ታውቋል።

የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ1.4 በመቶ ጨምሮ በእስያ ገበያ አንድ በርሜል በ69.21 ዶላር [2220 ብር ገደማ] እየተሸጠ ይገኛል። የወርቅ ዋጋም ቢሆን ከሚሳዔል ጥቃቱ በኋላ መናር መጀመሩ ታውቋል።

መካከለኛው ምስራቅ ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ ከተሰጋው ቀውስ ጋር በተያያዘ፣ የዓለም አቀፍ ገበያዎች የአክሲዮን ዋጋ በተቃራኒው እየቀነሱ መምጣታቸው ተነግሯል።

የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ጥቃቱ አሜሪካ ጄኔራል ቃሲም ሶሌይማንን በመግደሏ ለሱ ምላሽ ይሆን ዘንድ ነው ብሏል።

አርብ ዕለት በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት የተገደሉት ሱሌይማኒ ቀብር በትላንትናው ዕለት ከተፈፀመ ከሰዓታት በኋላ ነው ኢራን ሚሳዔሏን ወደ አሜሪካውያን መንደር የላከችው።

የሰውዬው ሞት በኢራንና ዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን ውጥረት አጡዞት ነገሮች ወደሌላ አቅጣጫ እንዳያመሩ ስጋት ጭሯል።

በዓለማችን እጅግ በርካታ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ የውቅያኖስ ውስጥ ነዳጅ ማሳለጫ በሁለቱ ሃገራት ውጥንቅጥ ችግር እንዳያጋጥመውም ተሰግቷል።

ሳዑዲ አራቢያ፣ ኢራቅ፣ ዩናይትድ አራብ ኤሜሬትስ እና ኩዌትን የመሳሰሉ ነዳጅ አውጭና ሻጭ ሃገራት በኢራንና አሜሪካ ግርግር ምክንያት ምጣኔ ሃብታቸው እንዳይጎዳም ስጋት አለ።

ኢራንም ቢሆን ለነዳጅ ሽያጯ የምትጠቀመው መስመር የሆርሙዝ ማሳለጫን ነው።

የዓለማች ግዙፍ የተጣራ ነዳጅ አምራች የሆነችው ካታርም ብትሆን የሆርሙዝ ማሳለጫን በመጠቀም ነው ነዳጇን የምትቸበችበው።

ከሚሳዔል ጥቃቱ በኋላ የአሜሪካ አየር ትራንስፖርት ባለሥልጣን አውሮፕላኖች በኢራን፣ ኢራቅና በአካባቢው የአየር ክልል እንዳይበሩ አስጠንቅቋል። ዕገዳው ኦማን እና ሳዑዲ አራቢያንንም የሚያካትት ነው።

አሁን ከተባባሰው የኢራንና አሜሪካ ውጥረት በፊትም ቢሆን የአሜሪካ አውሮፕላኖች ኢራቅ ውስጥ ከ26 ሺህ ጫማ በታች እንዲበሩ አይፈቀድላቸውም ነበር።

ከአሜሪካ በተጨማሪ የሲንጋፖር አየር መንገድ የኢራንን ሰማይ ይጠቀሙ የነበሩ አውሮፕላኖች ሌላ አቅጣጫ እንዲፈልጉ አሳስቧል።